በሱዳን ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ 7 ሰዎች ሞቱ
ከ140 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የሱዳን የጤና ሚኒስትር አመራሮች አስታውቀዋል
በሱዳን በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ተከትሎ በርካቶች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል
ትናንት ሌሊት በርካቶች “መፈንቅለ መንግስት” ነው ባሉት የሱዳን ጦር እርምጃ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሚኒስትሮች መታሰራቸው ይታወቃል።
በጦሩ እርምጃ የተናደዱት በርካታ ሱዳናውያን ወደ ካርቱም አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩ ሲሆን፤ ተቃውሞዎቹ ወደ ግጭት እየተለወጡ መምጣታቸውም ተሰምቷል።
የተቃውሞ ሰልፎቹን ወደ አመፅ መለወጣቸውን ተከትሎ የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር የስራ ኃላፊዎች አስታውቀዋል።
ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪም ከ140 ሰዎች በላይ መቁሰላቸውም አስታውቀዋል።
እንደ ሱዳን ጤና ሚኒስትር ኃላፊዎች ገለጻ፤ ህይወታቸው ያለፈው እና የቆሰሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች በጥይት ተመትው እንደሆነ በመግለፀ፤ አንድ ሰው ደግሞ በመኪና መገጨቱን ገልፀዋል።
የሱዳን ጦር የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ማሰሩን ተከትሎ፤ የሲቪል አስተዳሩ አባላት ሱዳናዉያን ተግባሩን ተቃውመው ወደ አደባባይ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የሱዳን ጦር በሲቪል አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ትናት በሰጡ መግለጫ፤ በሀገሪቱ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ቢገልጹም፤ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ግን አልተናገሩም።
ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን አክለውም፤ የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት የፈረሰ መፍረሱን እንዲሁም የክልሎች አሰተዳዳሪዎች እና ሌሎች አመራሮች ከስልጣን ተነስተዋል መነሳታቸውንም አስታውቀዋል።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ጉዳዩን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር መንግስቱን በወታደራዊ ቁጥጥር ስር መዋሉን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
የአፍሪከ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሱዳን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው፤ ጉዳዩ በንግግር እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በዛሬው እለት በሱዳን ጉዳይ ላይ እንደሚመከርም ተሰምቷል።