በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ከፊል የስምምነት ሰነድ እንደማትፈርም ሱዳን አስታውቃለች
በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ከፊል የስምምነት ሰነድ እንደማትፈርም ሱዳን አስታውቃለች
የሱዳን የመስኖና የዉሃ ሀብት ሚኒስቴር ዛሬ ግንቦት 04/2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በሚቀጥለው ሀምሌ ወር ግድቡን ዉሃ ስለመሙላት ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን ከፊል የስምምነት ሰነድ ሱዳን እንደማትቀበል ይፋ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያን አዲስ ሰነድ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መልእክት እንደተላከላቸው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
“በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ብቻ የግድቡ ሙሌት እንዲጀመር ሱዳን አትደግፍም” ያለው የሱዳን የመስኖና የዉሃ ሀብት ሚኒስቴር፣ ሙሌቱ ከመጀመሩ በፊት ግብጽን ጨምሮ በሶስቱ ሀገራት መካከል ስምምነት መደረስ አለበት ብሏል፡፡
በመሆኑም ሱዳን በመጪው ሐምሌ ወር የሚጠበቀው የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የዉሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት በካርቱም ፣ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል የሦስትዮሽ ስምምነት መድረስ አስፈላጊነትን በተመለከተ ጽኑ አቋም እንዳላት መግለጫው ያትታል፡፡
ሚኒስቴሩ አክሎም “ስምምነት ውስጥ መካተት ያለባቸው ቴክኒካዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች፣ የትብብር አሠራር ፣ የመረጃ ልውውጥ ፣ የግድቡ ደህንነት፣ አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖዎችን የተመለከቱ ጉዳዮች ምላሽ ሳያገኙ የሱዳን እና ኢትዮጵያ ከፊል ስምምነት ሊጸድቅ አይችልም” ብሏል፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ በመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች አማካይነት ድርድር ለማድረግ ባያስችልም ፣ በዲጂታል ኮንፈረንስ ፣ በ “ቪዲዮ ኮንፈረንስ” እና በሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮች አማካኝነት የድርድር ሂደቱን በማጠናቀቅ ስምምነት ባልተደረሰባቸው በቀሪዎቹ ነጥቦች መስማማት እንደሚቻል ሱዳን ያላትን አቋም ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጪው ሀምሌ ግድቡን ዉሃ ለመሙላት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ ሙሌቱ በመጪው ሀምሌ ወር እንደሚጀመር፣ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በተደረገ ግድቡን የተመለከተ ውይይት ላይ፣ መግለጹ ይታወቃል፡፡
ግብጽ የህዳሴ ግድብ በየዓመቱ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሄም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል ስጋት አላት፡፡ ከግድቡ የዉሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሶስቱ ሀገራት መካከል የመጨረሻ ስምምነት ሳይደረስ የዉሀ ሙሌት እንዳይጀመር የሚል መግለጫ፣ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ግምጃ ቤት መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ግብጽ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ አቤቱታ ከሰሞኑ ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርባለች፡፡