ሱዳን በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደርን ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠራች
አምባሳደር ይበልጣል አውሮፕላኑ በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ መግባን በካርቱም ለመገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል
ሱዳን አምባሳደሩን የጠራችው ኢትዮጵያ “በሱዳን በኩል የአየር ክልሌን ጥሶ የገባ አውሮፕላን መትቼ ጣልኩ” ማለቷን ተከትሎ ነው
ሱዳን በካርቱ የሚገኙተን የኢትዮጵያ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠራች።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ባሳለፍነው ሳምንት በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን አየር ክልል በመጣስ በህወሓት ቁጥጥር ስራ ወዳሉ የትግራይ ክልል እየበረረ የነበር አውሮፕላን መመታቱን ተናግረው ነበር።
በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደርን ይበልጣል አዕምሮ ከሰሞኑ በካርቱም በሰጡት መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስቴር ያወጣው መረጃ ትክክል መሆኑን ለሱዳን ብዙሀን መገናኛዎች አረጋግጠዋል ተብሏል።
ይሄንን ተከትሎም የሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮን ለተጨማሪ ማብራሪያ መጥራቱን ቡካርቱም ያለው የአል ዐይን ዘጋቢ አረጋግጧል።
በሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ፋድል አብዱላሂ በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደር የሱዳንን ስም አጥፍተዋል ሲሉ ከሰዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም "አምባሳደር ይበልጣል ያልተገባ ነገር ለሱዳን ብዙሀን መገናኛዎች ተናግረዋል፣ ንግግራቸውም የኢትዮጵያ እና ሱዳንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያበላሻል" ብለዋል።
በተለይም ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማስተካከል እየጣሩ ባለበት ባሁኑ ወቅት አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የተናገሩት ንግግር የሱዳንን ብሄራዊ ህግ የሚጥስ ነውም ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በሱዳን የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ መቀመጫቸውን ካርቱም ለሚገኙ ብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
በመግለጫው ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን በመተው ጦርነት በጀመረውና በሽብረተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ላይ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቅርበዋል።
ተቋርጦ ረጅም ወራትን ስላስቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ የተጠየቁት አምባሳደር ይበልጣል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ስር ወደሚካሄድ የሶስትዮሽ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።