የመከላከያ ሠራዊት የጦር መሳሪያ ጭኖ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ የገባ አውሮፕላን “መትቼ ጣልኩ” አለ
አውሮፕላኑ በሱዳን በኩል የኢትጵያን አየር ክልል ጥሶ በሁመራ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ ነበር
ንብረትነቱ የማን እንደሆነ ያልታወቀው አውሮፕላኑ ለህወሓት የጦር መሳሪያ ጭኖ እንደነበረ መከላከያ አስታውቋል
ለህወሓት የጦር መሳሪያ ጭኖ በሱዳን አልፎ የኢትዮያን አየር ክልል ጥሶ የገባ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን በሀገር መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሱዳን አድርጎ የኢትዮጵያን የአየር ክልልጥሶ በሁመራ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ የነበረና አውሮፕላን በአየር ኃይል ተመትቶ ወድቋል።
ንብረትነቱ የማን እንደሆነ ያልታወቀ አውፕላኑ ለህወሓት የጦር መሳሪያ ሊያቀብል እንደነበረም ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው አስታውቀዋል።
ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አክለውም “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስደፈር የሽብር ቡድኑን እየጋለቡ ያሉ ሃይሎች ቢኖሩም፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ኢትዮጵያውያነ ሀገራቸውን ለማስክበር በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል።
ላለፉት በርካታ ወራት ከፍኛ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው አሸባሪው ህወሃት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ኃይሉን ለውጊያ ሲያስጠጋ እንደነበረም የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊው አስታውቀዋል።
በህወሓት ትናንትናው ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት 11 ሰዓት ላይ በቆቦ ግራና ቀኝ ባሉ አካባቢዎች፣ በዞብል ተራራ፣ በቢሶበርና በወትወት ውጊያ መክፈቱንም ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑም ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውን ጦርነት መጀመሩን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃይሎች ትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል፡፡
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል፡፡ ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡