የአልበሽር ደጋፊዎች ከያሉበት እንዲታደኑ እና ክስ እንዲመሰረትባቸው ውሳኔ ተላልፏል
በሱዳን የተለያዩ አካባቢዎች ለተቀጣጠለው አመጽ የኦማር አልበሽር ደጋፊዎችን ተጠያቂ ያደረገችው ሱዳን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፓርቲ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ወስናለች፡፡
የፕሬዝዳንት አልበሽርን ደጋፊዎች መረብ ለመበጣጠስ የተቋቋመው ኮሚቴ በሀገሪቱ የተፈጸመውን አመጽ አስተባብረዋል በሚል የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ከያሉበት እንዲታደኑ እና ክስ እንዲመሰረትባቸው ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የኮሚቴው ድንጋጌ የክልል ገዥዎች በዐቃቤያን ሕግ በኩል “የተበተነው የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች በሙሉ እንዲሁም አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙ የፓርቲው ካድሬዎቹ እና አመራሮች” ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ያዛል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ ጄኔራሎች እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2019 ኦማር አል በሽርን ከስልጣን ያስወገዱ ሲሆን አሁን ላይ የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የመሰረቱት የሽግግር መንግስት በብዙ ፈተና ውስጥ ይገኛል፡፡
ከዳቦ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ካርቱምን ጨምሮ በሱዳን በርካታ ስፍራዎች ላይ በተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍ የመንግስት ህንጻዎች እና ተሽከርካሪዎች በእሳት ሲቃጠሉ ሌሎች በርካታ ንብረቶችም ወድመዋል ፤ ዘረፋዎችም ተፈጽመዋል፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር በሀገሪቱ በትንሹ 7 ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው የተቃውሞ እንቅስቃሴው በዋጋ ንረት ፣ በዳቦ እና በነዳጅ ከፍተኛ እጥረት ፈተና በገጠመው በሽግግሩ መንግስት ላይ የሚደረግ “የኢኮኖሚ ጦርነት” እንደሆነ ነው የአልበሽርን መረብ እንዲበጣጥስ የተቋቋመው ኮሚቴ የገለጸው፡፡
ባለፈው ሳምንት የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሌሎችም የቀድሞ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡ በሀገሪቱ አሁንም ህዝባዊው ተቃውሞው መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡