ከአፍሪካ ህብረት የታገደችው ሱዳን በግድቡ የድርድር ሂደት አትሳተፍም ተባለ
ህብረቱ፤ ሱዳን የሽግግር ሂደቱን ይመራ የነበረው የሲቪል አስተዳደር ወደ ቦታው እስከሚመለስ ድረስ ታግዳ እንደምትቆይ ማስታወቁ ይታወሳል
ይህ የተባለው የአፍሪካ ህብረት ሱዳን በየትኞቹም የድርጊት መርሃ ግብሮቹ እንዳትሳተፍ ማገዱን ተከትሎ ነው
ሱዳን በአፍሪካ ህብረት መታገዷን ተከትሎ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደት ላይ እንደማትሳተፍ ተገለጸ፡፡
በየትኞቹም የድርጊት መርሃ ግብሮቹ እንዳትሳተፍ በህብረቱ የታገደችው ካርቱም አፍሪካ ህብረት መር በሆነው የግድቡ የድርድር ሂደት እንደማትሳተፍ የህብረቱ የአል ዐይን አማርኛ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
አፍሪካ ህብረት፤ የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ ካርቱም ከአባልነት ታግዳ እንደምትቆይ አስታወቀ
እገዳው በሁሉም የህብረቱ እንቅስቃሴዎች ማለቱን ያስታወሱት ምንጮቹ እገዳው በህብረቱ የሚመራውን የግድቡን የድርድር ሂደት እንደሚመለከት ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ካርቱም በግድቡ የድርድር ሂደት መሳተፍ አትችልም ብለዋል፡፡
ይህ ልክ የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት እንዳሳለፈው ውሳኔ ሁሉ የሽግግር ሂደቱን ይመራ የነበረው የሲቪል አስተዳደር ወደ ቦታው እስከሚመለስ ድረስ የሚቀጥል ነው እንደ ምንጮቹ ገለጻ፡፡
ካርቱም በህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ፕሮቶኮል አንቀጽ 7 መሠረት ነው ከአባልነት የታገደችው፡፡
እገዳው በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሱዳን የሲቪል መንግስት በሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው የሃገሪቱ ጦር ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ የተጣለ ነው፡፡
ሃገሪቱን ከእርስበእርስ ጦርነት ለመታደግ በሚል እርምጃውን መውሰዳቸውን የገለጹት ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሃምዶክ የሚመራውን የሲቪል መንግስት ጨምሮ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ እንዲሁም ሌሎች የሙያ ማህበራት መበተናቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የሚደረገው ድርድር በቶሎ ሊጀመር በሚችልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከተደራዳሪ ሃገራቱ ጋር መምከሯ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ፤ በዲ.አር.ሲ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ወደ ድርድሩ ለመመለስ ያላትን ቁርጠኝት መግለጿ አይዘነጋም፡፡