በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከእስር ተለቀቁ
አሜሪካንን ጨምሮ መፈንቅለ መንግስትቱን ያወገዙ በርካታ አገራት ጦሩ ያሰራቸውን ሌሎች ሰዎች እንዲለቅ አሳስበዋል
ሃምዶክ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ጋር በስልክ አውርተዋል
በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከእስር ተለቀቁ፡፡
ከትናንት በስቲያ በካርቱም በጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር በአገሪቱ ሲቪል አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
በዚህ መፈንቅለ መንግስት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሀምዶክ ከስልጣናቸው ተነስተው ባልታወቀ ስፍራ መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡
የሱዳን ጦር፤ ትናንት ከቡርሃን የመከሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ለምን አሰረ?
ሀምዶክ ትናንት ምሽት ከታሰሩበት ስፍራ ወደመኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በስልክ አውርተዋል፡፡
ወሬውን የተመለከተ ጽሁፍ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ብሊንከን በሀምዶክ መፈታት መደሰታቸውን ገልጸው አሁንም በእስር ላይ ያሉ ሌሎች የሲቪል አስተዳደር አመራሮች እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለ
በሱዳን መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙን ተከተሎ ድርጊቱን የተቃወሙ ሱዳናውያን ወደ አደባባዮች በመውጣት መንገዶችን እየዘጉ ሲሆን አለመረጋጋቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ “ለደህንነታቸው ሲባል” በቤታቸው መሆናቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
ጀነራሉ አክለውም በመላው ሱዳን የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን፣ የሱዳን ሲቪል አስተዳደር፣ ምክር ቤቶች እና ሌሎች መፍረሳቸውን እና ምርጫ አስከሚካሄድ ድረስ አገሪቱ በወታደራዊ አመራሮች እንደምትመራም ገልጸዋል፡፡
አክለውም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎች በእስር ቤት እንደሚቆዩ ገልጸው፤ ሌሎቹ ግን ከእስር ይለቀቃሉ ብለዋል።