በርካታ ሱዳናውያን ወታደራዊ አገዛዝን በመቃወም ወደ አደባባዮች ወጥተዋል
የሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም ዛሬም በተቃውሞ ስትናጥ ነው የዋለችው፡፡
በሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራውን ወታደራዊ አገዛዝ በመቃወምም ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ በርካታ ሱዳናውያን የካርቱምን ጎዳናዎች አጥለቅልቀዋል፡፡
መዳኒ እና አጥባራን በመሳሰሉ ሌሎች ከተሞችን የተቃውሞ ሰልፎች አሉ፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት በፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን አሰናብቶ ቁም እስረኛ አድርጓው የነበሩትን አብደላ ሃምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የመለሰው ወታደራዊ አገዛዙ የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይካሄድ ለማድረግ ጥሮ ነበር፡፡
የሰልፍ ጥሪ የሚደረግባቸው የስልክ ጥሪዎችን ጨምሮ የኢንተርኔት ግንኙነትን ለስድስት ያህል ሰዓታት አቋርጦ ነበር፡፡
የጸጥታ ኃይሎቹን አሰማርቶ ካርቱምን ከኦምዱርማን የሚያገናኙ ድልድዮችን ጨምሮ ዋና ዋና መተላለፊያዎችን ለመዝጋትም ሞክሯል፡፡
ወደተከለከሉ ስፍራዎች እና ጥብቅ መንግስታዊ ተቋማት እንዳይጠጉም አሳስቦም ነበር፤ ይህን ተላልፈው በሚገኙት ላይ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በማሳሰብ፡፡
ሆኖም መቃወማቸውን እንደሚቀጥሉ ቀደም ሲልም ያስታወቁት ሰልፈኞች ዛሬም በሺዎች ሆነው ወደ አደባባዮች ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ብሔራዊ ቤተመንግስት አካባቢ ለመገናኘት በማሰብም በተለያዩ አቅጣጫዎች ይጓዙ ነበር እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ፡፡
ሰልፈኞቹ በጥብቅ ወደሚጠበቁት ተቋማት እንዳይጠጉ ለማድረግ የጸጥታ አካላቱ አስለቃሽ ጋዝን በመጠቀም ጭምር ሲበትኑ እንደነበርም የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን እስካሁን የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም፡፡
የዛሬ ሳምንት እሁድ በቤተ መንግስቱ አቅራቢያ የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሰልፈኞችን ለመበተን በተወሰደ እርምጃ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ እና ከ300 የሚበልጡ ሰዎች መጎዳታቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተገደው የተደፈሩ አሉ የሚል ክስ ማቅረቡም የሚታወስ ነው፡፡