የሃምዶክ ወደ ስልጣን መመለስ የሱዳንን ፖለቲካዊ ቀውስ አልገታውም- ተመድ
በሌ/ጄ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሃምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መመለሱ የሚታወስ ነው
በጦሩ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተደረሰው ስምምነት የተሟላ እንዳልሆነም መልዕከተኛው ገልጸዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን መልዕክተኛ የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ገና አልተቋጨኝ ሲሉ ተናገሩ፡፡
መፈንቅለ መንግስትን ያካሄደው የሃገሪቱ ጦር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ባደረገው ስምምነት ሃምዶክ ወደ ስልጣናቸው ቢመለሱም ስምምነቱ በብዙዎች ዘንድ የመከዳት ስሜት መፍጠሩን ልዩ መልዕክተኛው ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በርካቶች አሁንም ወደ አደባባዮች በመውጣት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው እንደ መልዕክተኛው ገለጻ፡፡
ሱዳናውያኑ ወታደር መር በሆነው ፖለቲካዊ አካሄድ ተበሳጭተዋል ያሉት ቮከር ፔርዝስ በፈረንጆ 2019 የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ አስቀጥሎ ከግብ የማድረስ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው ጦር ሃምዶክን እና ሌሎች የሲቪል መንግስት ባለስልጣናትን በማሰር ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ካሳለፍነው ጥቅምት 25 ጀምሮ ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡
ፖለቲካዊ ቀውሱ አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት ቮከርም በጦሩ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተደረሰው ስምምነት ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለማስቀረት ቢችልም የተሟላና የተዋጣለት የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የጦሩን እርምጃ በመቃወም ወደ አደባባዮች በወጡ ሱዳናውያን ላይ በተወሰደው እርምጃ 44 ያህል ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጎዳታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡