የየመኑ ታጣቂ ቡድን ዛሬ በቀይ ባህር 26ኛ የጥቃት ሙከራውን ነው ያደረገው
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የጥቃት ሙከራዎችን ማድረጉ ተነገረ።
በጥቃቶቹ እስካሁን የደረሰው ጉዳት ባይገለጽም ከእስካሁኖቹ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት ሙከራዎች ሁሉ ግዙፍ ነው ተብሏል።
አምብሬይ የተሰኘው የደህንነት ተቋም እንዳስታወቀው ድሮኖቹና ሚሳኤሎቹ የተተኮሱት ከየመን የወደብ ከተሞቹ ሁዴይዳ እና ሞክሃ ነው።
በቀይ ባህር ሲጓዙ የነበሩ መርከቦች በሬዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ድሮኖችና ሚሳኤሎችን መመልከታቸውን ሲገልጹ ይደመጣል ያለው አምብሬይ፥ የአሜሪካ መራሹ የባህር ቅኝት ግብርሃይል መርከቦቹ በመጨረሻው ፍጥነታቸው እንዲያመልጡ ማሳሰቡንም ያክላል።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝም በሃውቲዎች የተቃጣው “ውስብስብ ጥቃት” ቦምብ የተሸከሙ ድሮኖችን፣ ጸረ መርከብ ክሩዝ ሚሳኤሎች እና ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ያካተተ እንደነበር ገልጿል።
በቀይ ባህር የሚገኙ የአሜሪካ ግዙፍ ወታደራዊ መርከቦችም የቡድኑን 18 ድሮኖች፣ ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎች እና ጸረ መርከብ ባለስቲክ ሚሳኤል በመምታት ጥቃቱን ማክሸፉን ነው እዙ ያስታወቀው።
የዛሬው ግዙፍ የጥቃት ሙከራ የሃውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የፈጸሙት 26ኛው ጥቃት ነው የተባለ ሲሆን፥ ቡድኑ ጥቃቱን ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ አልሰጠም።
በኢራን ለሚደገፈው ቡድን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጠችው አሜሪካ የጸጥታው ምክርቤት ሀገራት መርከቦቻቸውን ከሃውቲ ታጣቂዎች ለመጠበቅ እርምጃ እንዲወስዱ መፍቀድ አለበት ብላለች።
ዋሽንግተን ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት አለማቀፉን ህግ ተከትለው መርከቦቻቸውንና ነጋዴዎቻቸውን ለመጠበቅ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል።
ይሁን እንጂ በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ተካቶ የነበረው ሀገራት እርምጃ የመውሰድ መብት አላቸው የሚለው ነጥብ ተቀንሶ ዛሬ ለጸጥታው ምክርቤት ይቀርባል መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።