ግብጽ የስዊዝ ካናል አመታዊ ገቢ በ25 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገለጸች
ካይሮ ከስዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ቅናሽ ማሳየቱን ነው ይፋ ያደረገችው
በመተላለፊያው የተጓዙ መርከቦች ቁጥርም ካለፈው አመት በ5 ሺህ ዝቅ ያለ መሆኑን አስታውቃለች
ግብጽ የስዊዝ ካናል አመታዊ ገቢ በ25 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገለጸች።
የስዊዝ ካናል ባለስልጣን ሃላፊው ኦስማን ራቢ በዛሬው እለት ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት ካይሮ በ2023/24 በጀት አመት ከመተላለፊያው ያገኘችው ገቢ 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ነው።
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ቅናሽ ያለው መሆኑን ሃላፊው መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የየመኑ ሃውቲ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን መቀጠሉ ይታወቃል።
ቡድኑ ከእስራኤል፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ ከ60 በላይ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት ፈጽሙ ሁለት መርከቦችን ማስመጡና አንድ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሉ አይዘነጋም።
አሜሪካና ብሪታንያም በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ከ400 በላይ የአየር ጥቃቶችን ቢፈጽሙም የቀይ ባህርን የመርከቦች ጉዞ ሰላማዊነት ማረጋገጥ አልቻሉም ነው የተባለው።
የስዊዝ ካናል ባለስልጣን ሃላፊው ኦስማን ራቢ በ2023/24 በካናሉ 20 ሺህ 148 መርከቦች ማለፋቸውን ገልጸዋል።
ይህ አሃዝ ካለፈው አመት በ5 ሺህ 763 ዝቅ ማለቱም የጦርነቱን ዳፋ አለመቆም አመላካችነት አብራርተዋል።
የግብጽ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆነው ስዊዝ ካናል ከ2015 ጀምሮ ማስፋፊያ እየተደረገለት በየአመቱ 10 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ሲያስገኝ ቆይቷል።
ዘጠኝ ወራት ያለፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ግን የንግድ መርከቦች አቅጣጫቸውን ለውጠው ረጅሙን የደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ የንግድ መስመር እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል።
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ ካላቆመች ጥቃቴ ይቀጥላል ያለው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን አውሮፓና እስያን በሚያስተሳስረውና ከአለማችን ሸቀጥ 15 በመቶው በሚተላለፍበት የስዊዝ ካናል ደህንነት ላይ ስጋት ደቅኗል።
የንግድ መርከቦች መተላለፊያውን መጠቀማቸውን መቀነሳቸውና ረጅሙን የንግድ መስመር ለመከተል መገደዳቸው የአለም የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ ተነግሯል።