ባርሴሎና ደግሞ የአርቢ ላይፕዚሹን ዳኒ ኦልሞ ለስድስት አመት ለማስፈረም ለጀርመኑ ክለብ እቅዱን ማስገቱ ተሰምቷል
የአውሮፓ ክለቦች በቀጣዩ የውድድር አመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ነው።
ባለፈው የውድድር አመት 8ኛ ሆኖ ያጠናቀቀውና ፈረንሳዊውን ወጣት ተከላካይ ሌኒ ዮሮ ያስፈረመው ማንቸስተር ዩናይትድ ብራዚላዊውን አንቶኒ በውሰት ለመልቀቅ መዘጋጀቱ ተሰምቷል።
አንቶኒን በውሰት የሚወስድ ክለብ ለተጫዋቹ በየሳምንቱ 70 ሺህ ፓውንድ መክፈል ግን ይጠበቀበታል መባሉን የአሜሪካው ኢኤስፒኤን ዘግቧል።
ባርሴሎና ደግሞ ስፔናዊውን የአርቢ ላይፕዚሽ አማካይ ዳኒ ኦልሞ ለስድስት አመት ለማስፈረም እቅዱን ለጀርመኑ ክለብ ማስገባቱን የስፔኑ ሙንዶ ዲፖርቲቮ ጋዜጣ አስነብቧል።
የአያክሱን ግብ ጠባቂ ቶሚ ሴትፎርድ ለማስፈረም ተቃርቧል የተባለው አርሰናል በበኩሉ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ የደመቀውን ስፔናዊ ኒኮ ዊሊያምስ በ47 ሚሊየን ፓውንድ ለማስፈረም ከሌሎች ክለቦች ጋር ፉክክሩን መቀጠሉ ተሰምቷል።
መድፈኞቹ እንግሊዛዊውን አማካይ ኢሚሊ ስሚዝ ሮው ለማስፈረም ከክሪስታል ፓላስ ጋር ፉክክር ውስጥ ገብተዋል ብሏል ቶክ ስፖርት በዘገባው።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በዚህ የክረምት የዝውውር መስኮት የ20 አመቱን ፈረንሳዊ አማካይ ሌስሊ ኡጎቹኩ በውሰት እንደሚለቅ ደግሞ ዘ አትሌቲክ ዛሬ ይዞት የወጣው ዘገባ ያሳያል።
አዲሱ የቼልሲ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ የዝውውር መስኮቱ ሳይዘጋ ስፔናዊውን ሮበርት ሳንቼዝ የሚተካ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል ዘገባን ያወጣው ደግሞ ቴሌግራፍ ነው።
ሰማያዊዮቹ የናፖሊውን ቪክቶር ኦስምሄን ለማስፈረም አሁንም ፍላጎት ቢኖረውም ፒኤስጂ ግን ናይጀሪያዊውን አጥቂ ለማስፈረም ቀዳሚ ግምት ተሰጥቶታል።
የርገን ክሎፕን በአርኔ ስሎት የተካው ሪቨርፑል ደግሞ አየርላንዳዊውን ግብ ጠባቂ ኬልሄር ለመሸጥ መዘጋጀቱን ፉትቦል ኢንሳይደር አስነብቧል።
ቀያዮቹ ሆላንዳዊውን ተከላካይ ዲን ሁጅሰን ከጁቬንቱስ ለማስፈረም ከኒውካስትል ጋር እየተፎካከሩ ቢሆንም የጣሊያኑ ክለብ ያቀረበው 25 ነጥብ 3 ሚሊየን ፓውንድ ዋጋ ፊቷን ወደሌላ ተጫዋች እንዲያዞር ሊያደርገው ይችላል ብሏል የጣሊያኑ ቱቶስፖርት።
ቶትንሃም ብራዚላዊው አጥቂ ሪቻርልሰን ወደ ሳኡዲ ክለቦች እንዲዘዋወር ፈቃዱን መሰጠቱንና ለዝውውሩ 60 ሚሊየን ፓውንድ እንደሚጠይቅ ኤችአይቲሲ የተሰኘው የስፖርት ድረገጽ ዘግቧል።
ዛሬ ከተሰሙ የዝውውር ጭምጭምታዎች ውስጥ ክሪስታል ፓላስ የ26 አመቱን ሴኔጋላዊ አጥቂ ኢስማኤላ ሳር ለማስፈረም ከማርሴ ጋር ንግግር ጀምሯል የሚለው የዘ አትሌቲክ ዘገባም ይገኝበታል።
ታዋቂው ጣሊያናዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ደግሞ ብራይተን ጀርመናዊውን አጥቂብራጃን ግሩዳ ከሜንዝ ለማስፈረም ድርድሩን መቀጠሉን ይፋ አድርጓል።
የዘንድሮው የክረምት ዝውውር መስኮት በጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ሃምሌ 1 የተከፈተ ሲሆን፥ በእንግሊዝ ከሃምሌ 14 ጀምሮ ክፍት ሆኗል። የዝውውር መስኮቱ በአምስቱም ዋና ዋና ሊጎች ነሃሴ 30 2024 ይጠናቀቃል።