የላሊበላ ሰማይ ሰኔ አጋማሽ ላይ ለተወሰኑ ሴኮንዶች ይጨልማል
ወርሃ ሰኔ አጋማሽ ላይ ቀለበታዊ የፀሀይ ግርዶሽ ላሊበላ አካባቢ ይከሰታል ተባለ
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመጪው ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ቀለበታዊ የፀሀይ ግርዶሽ ላሊበላ አካባቢ እንደሚከሰት አስታውቋል፡፡
ግርዶሹ ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በተለይም ላሊበላ አካባቢ ከማለዳው 12 ሰዓት ከ45 ጀምሮ እስከ 6 ሰዓት ከ33 ድረስ እንደሚቆይም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ገልፀዋል፡፡
ወለጋ፣ ከፊል ጎጃምና ጎንደርም የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡በፓኪስታን፣ በህንድ እና በማዕከላዊ አፍሪካ እንደሚታይም ነው የተናገሩት፡፡
በእለቱም ከረፋዱ 3 ሰዓት ከ40 አካባቢ ለተወሰኑ ሴኮንዶች ጨለማ እንደሚፈጠር የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሚታወቅ ነው፤ኢትዮጵያ በከስተቱ ከሚመራመሩ የአለም ሳይንቲስቶች ከሚገኘው እዉቀት ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡
ስለሆነም ክስተቱን መመልከት የሚፈልግ ሁሉ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በንቃት ጠብቆ እንዲከታተል ዶ/ር ሰለሞን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዝርዝር ሳይንሳዊ አንድምታዎች በየጊዜው እንደሚገለጹ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ማስታወቁንም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡