አንቀጾቹ በዋናነት የምክር ቤቱን የስልጣን ዘመንና የአመራረጥ ሁኔታ እንዲሁም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚመለከቱ ናቸው
ምክር ቤቱ ይተርጎሙ ያላቸው ሦስት አንቀጾች ምን ይላሉ?
በመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሃገራዊውን ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ባሳለፍነው ሳምንት ያጸደቀው ምክር ቤቱ የምርጫውን አለመካሄድ ተከትሎ ሊኖሩ የሚችሉ ቀጣይ ህገመንግስታዊ የመፍትሄ ሀሳቦች ምን እንደሆኑ መርምሮ እንዲያቀርብ ጉዳዩን ወደ ህግ፣ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶ ነበረ፡፡
በተመራለት መሰረት ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ቋሚ ኮሚቴውም መፍትሄ ያላቸውን ህገመንግስታዊ ሃሳቦች አቅርቧል፡፡
ምርጫን በተመለከተ በህገ መንግስቱ ሶስት አንቀጾች ላይ ትርጓሜ ይሰጥ የሚል የመፍትሄ ሃሳብንም ነው ኮሚቴው ያቀረበው።
ከህገ መንግስት አላማ እና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆች ጋር ለማስተሳሰር ትርጉም ይሰጥባቸው በሚል የቀረቡት አንቀጾችም አንቀፅ 54/1፣አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 93 ናቸው።
በቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን የሰነዘሩት የምክር ቤቱ አባላትም በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ሃሳቡን አጽድቀዋል፡፡
ለመሆኑ የተጠቀሱት ሶስት አንቀጾች ምን የሚሉ ናቸው?
ቀዳሚዎቹ ሁለት አንቀጾች (አንቀፅ 54/1 እና አንቀፅ 58/3) ስለ ፌዴራሉ ምክር ቤቶች በሚያተትተው የህገ መንግስቱ 6ኛ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡
የፌዴራሉ መንግስት የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን የተሰኙ ሁለት ምክር ቤቶች እንዳሉት የሚያትተውን አንቀጽ 53ን ተከትሎ የሰፈረው የምዕራፉ የመጀመሪያ ክፍልም (ክፍል አንድ) የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የተመለከቱ 7 አንቀጾችን ይዟል፡፡
እነዚህ 7 አንቀጾችም የምክር ቤቱ አባላት የአመራረጥና የምክር ቤት የቆይታ ጊዜ እንዲሁም መብትና ተገዢነታቸውንም የሚደነግጉ ሃሳቦችን ይዘዋል፡፡
ቀደም ሲል በቋሚ ኮሚቴው የተጠቀሰው አንቀጽ 54ም ከነዚሁ አንቀጾች መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በክፍሉ የመጀመሪያ አንቀጽ ሆኖ ሰፍሮም ይገኛል፡፡ አንቀጹ የአባላቱን አመራረጥ በተመለከተ የሚያትት ነው፡፡
“የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ሁሉን አቀፍ፥ነፃ፥ቀጥተኛ፥ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ” የሚል ሃሳብንም ይዟል፡፡
ከምርጫው መራዘም ጋር በተያያዘ የስልጣን ዘመኑ መጠናቀቂያ ላይ የሚገኘው የምክር ቤቱና የአባላቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ተያይዘው የሚቀርቡ የህጋዊነት ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡
ይህ የትርጉም ጥያቄም ምናልባትም ለዚሁ ጉዳይ ምላሽ የሚሰጥ ሊሆንም ይችላል፡፡
በዚሁ ምዕራፍ ስር የሚገኘው አንቀጽ 58/3ም የምክር ቤቱን ስብሰባና የስራ ዘመን የሚመለከት ነው፡፡
የምክር ቤቱ ምልዓተ ጉባዔ የሚኖርበትን፣ለስብሰባ የሚጠራበትንና የሚያርፍበትን እንዲሁም የስራ ዘመኑ ከመቼ እስከ መቼ እንደሆነ ጭምር በወራትና ቀናት ከዚህ እስከዚህ ብለው የሚያስቀምጡ አምስት ንዑሳን አንቀጾችንም ይዟል፡፡
ኮሚቴው የህግ ትርጓሜ ያሻዋል በሚል ያቀረበው የአንቀጹ 3ኛ ንዑስ አንቀጽም ከነዚሁ አምስት ንዑሳን አንቀጾች መካከል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ንዑስ አንቀጹ የምክር ቤቱን የስራ ዘመን የሚደነግግ ሲሆን
“የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል” በሚል ተጽፎ ይገኛል፡፡
አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ይህ እንዲሆን የሚፈቅድ፤የሚያስችልም አይመስልም፡፡ የስልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የምክር ቤት አባላትን በህዝብ ነጻ ፍቃድ እና ይሁኝታ በተመረጡ አባላት ለመተካት የሚያስችለው ሃገራዊ ምርጫን የማካሂያዱ ውጥንም በኮሮና ምክንያት ችግር ላይ መውደቁ እውን ሆኗል፡፡ ይህ መሆኑን ተከትሎ የምክር ቤቱና የአባላቱ ህጋዊነት እና ቅቡልነት ተጠየቅ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ ከአሁኑ እየተስተዋለ ያለውም ይኸው ነው፡፡ለአንቀጹ የሚሰጡ ትርጓሜዎች ለዚህ ጉዳይ ምላሽ የሚገኝባቸው እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡
ሌላኛው ትርጓሜ የተጠየቀበት አንቀፅ 93 ደግሞ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን በያዘው የህገ መንግስቱ አስራ አንደኛ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ስለ አስቸኳይ ገዚ አዋጅ ያትታል፡፡ አዋጁ ሃገሪቱ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲገጥሟት፣በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ፣ በማን እንደሚታወጅ እና ምን እንደሚደረግም በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ የአዋጁን አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ እንዴት ባለ መልኩ ሊቋቋም እንደሚችልና ኃላፊነቱ ምን እንደሆነም በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡
ይህንኑ አንቀጽ ታሳቢ አድርጎም መንግስት ለ5 ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል ቦርድ ተቋቁሞም ወደ ስራ ገብቷል፡፡
ሆኖም መንግስት ምርጫውን ለማካሂያድ ድጋሚ አስቸኳይ ጊዜን ማወጅ ያስፈልገው እንደሆነ አማራጭ አድርጎ ቀርቧል፡፡ በአንቀጹ ላይ የተጠየቀው ትርጉም ለዚህ ምላሽ የሚሆን ነገርን ይዞ እንደሚመጣም ይጠበቃል፡፡
ለአንቀጾቹ ትርጓሜን የመስጠቱ ሂደት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ እና በምክትላቸው በሚመራው የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሚፈጸም ይሆናል፡፡