ምህረት ለማድረግ፣ የመከፈያ ጊዜን ለማራዘምና የሚከፍሉትን ለማበረታታት ተወስኗል
ኢትዮጵያ የግብር እዳዎችን ለማቅለል ወሰነች
ከዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የግብር ዕዳ ምህረት የማድረግ፣ የመከፈያ ጊዜ የማራዘምና የሚከፍሉትን የማበረታታት ውሳኔዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ውሳኔዎቹን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወሰነው መሰረት የወጣው መመሪያ ተግባራዊ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ውሳኔው በሁለት ምድብ ተከፍሎ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡
የመጀመሪያው ምድብ እስከ 2007 ዓ/ም ያለውን የግብር ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ምድብ ደግሞ ከ2008-2011 ዓ.ም ያለውን የግብር ዓመት የሚመለከት ነው፡፡
ሁለተኛው ምድብ ከ2008-2011 ዓ.ም ያለውን የግብር ዓመት ይመለከታል፡፡ በሶስት ዓይነት መንገድ የሚታይም ሲሆን የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ የደረሳቸው መቀጫ፣ ፍሬ ግብርና ወለድ ያለባቸው ከሆነ የፍሬ ግብሩን 25 በመቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከፍለው 75 በመቶውን በአንድ ዓመት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች መቀጫና ወለድ ተነስቶላቸዋልም፡፡
በሌላ በኩል በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ፍሬ ግብሩን ለሚከፍሉ ደግሞ 10 በመቶ ከፍሬ ግብሩ ተቀንሶላቸው መቀጫና ወለድ እንዲቀርላቸው ስለመወሰኑም ይፋ ሆኗል፡፡
በሁለተኛው ምድብ ውስጥ ገቢያቸውን አስታውቀው የከፈሉ ነገር ግን በተቋሙ ኦዲት ተደርጎ የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ያልደረሳቸው ግብር ከፋዮችን በሚመለከትም ውሳኔው ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡
በ30 ቀናት ውስጥ በኦዲት የተገኘውን የፍሬ ግብር 25 በመቶ ቅድሚያ በመክፈል ቀሪውን 75 በመቶ በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቆ መክፈል ለሚችል ቅጣትና ወለድ የሚነሳ ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ የፍሬ ግብሩን በሙሉ በሙሉ ለሚከፍል ደግሞ ወለድና ቅጣት ከማንሳት በተጨማሪ ከፍሬ ግብሩ 10 በመቶ ይቀነስለታል፡፡
ሌላው ገቢን አሳውቀው ክፍያ ያልጀመሩትን የሚመለከት ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ አሳውቀው ከከፈሉ በተመሳሳይ የምህረቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ውሳኔው ተፈፃሚ የሚሆነው ግብር ከፈዮች የጀመሩትን የታክስ ይግባኝ ወይም በየደረጃው ያሉ ክርክሮችን ካቋረጡ እና በውሳኔው መስማማታቸውን ግብር ለሚከፍሉበት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሲያመልክቱና ሲያሳውቁ ነው፡፡
ለሶስተኛ ወገን ያልተላለፈ ነገር ግን በታክስ ዕዳ ምክንያት የተያዘ ንብረት ካለ ድርጅቱ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መኖሩ ከተረጋገጠ እና ንብረቱ ተንቀሳቃሽ ከሆነ ዋስትና አቅርቦ የሚመለስበት አግባብ እንዳለም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡