አንቶኒ ብሊንከንና ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያዩ
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ አሜሪካና ኬንያ ድጋፍ ለማድረግም ተስማምተዋል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግጭት ላይ ያሉ ሁሉም አካላት በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መወያየታቸው ተገለፀ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “በኢትዮጵያ እየተባባሰ በመጣው ወታደራዊ ግጭቶች አሜሪካን እንደሚያሳስባት ለፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አሳውቄያለሁ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ግጭት የምስራቅ አፍሪከ ቀጠናን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በግጭቱ ውስጥ እየተሳፉ ያሉ ሁሉም አካላት የሀገሪቱን ሉአላዊነት እና አንድነት ባስጠበቀ መልኩ ወደ ሰላም ለመምጣት ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኒድ ፕራይስ ውይይቱን አመስመልክቶ በሰጡት መግለጫም፤ በውይይቱ ወቅት በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጡ አሜሪካ ጥሪ ማቅረቧን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ኬንያታ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በግጭቱ ለተጎዱ ማህበረሰቦች ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋ አቅርቦት አስፈላጊነት ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ አሜሪካ እና ኬንያ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር።
መንግስት ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል።
በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል።
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት በመሰንዘር፤ ሰዎች እንዲገደሉና በ2 ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንገስት ማስታወቁ ይታወሳል።
አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ተዳርገዋል ብሏል ክልሉ።
መንግስት በኢትዮጵያ በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።