በወረርሽኝ የተጠቁ ሌሎች ወፎችን ለማከም ጥረት መጀመሩን የሀገሪቱ መንግስት ገልጿል
በናሚቢያ የወፍ ጉናፋን እንደሆነ የተጠረጠረ ወረርሽኝ ከ200 በላይ ወፎችን ገደለ፡፡
በደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናሚቢያ የወፍ ጉንፋን ወረርሽኝ ተከስቶ ከ200 በላይ ወፎች ሞተው መገኘታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ የእንስሳት ጤና መምሪያ ከሞቱት ወፎች በተጨማሪ መታመማቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች ከሌሎች ወፎች ላይ መመልከቱን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ለወፎቹ መታመም እና መሞት መነሻ ምክንያቶችን ለማረጋገጠ ናሙና ወስዶ የቤተ ሙከራ ምርመራ በማካሄድ ላይ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ወፎቹን ላጠቃው ወረርሽኝ ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ወፎች ምክንያት ሳይመጣ እንዳልቀረ የሀገሪቱ መንግስት ጥርጣሬውን ጠቅሷል፡፡በመሆኑም ህብረተሰቡ የታመሙ ወይም የሞቱ ወፎችን ከመያዝ እና ከመመገብ እንዲታቀብ ይሄው ተቋም አስጠንቅቋል፡፡
ናሚቢያ የወፍ ጉንፋን በተደጋጋሚ የሚያጠቃት ሲሆን ከዚህ በፊት ዶሮ እና የዶሮ ምርቶች ከየትኛውም አገር ወደ ግዛቷ እንዳይገባ እገዳ እስከመጣል ደርሳ ነበር፡፡