ሱዙኪ በሃንጋሪ የሚገኘው ፋብሪካው ምርት ማቆሙን ገለጸ
የጃፓኑ ኩባንያ በቀይ ባህር ውጥረት ምክንያት ሞተርና ሌሎች ግብአቶች በፍጥነት እየደረሱኝ አይደለም በሚል ነው ምርቱን በጊዜያዊነት ያቋረጠው
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቹ ቴስላም በጀርመን የሚገኘው ፋብሪካው ለሁለት ሳምንት ምርት እንደሚያቆም ማሳወቁ ይታወሳል
በሃንጋሪ የሚገኘው የሱዙኪ ተሽከርካሪ ማምረቻ ፋብሪካ ከዛሬ ጀምሮ ምርቱን አቋርጧል።
የጃፓኑ መኪና አምራች ኩባንያ ቪታራ እና ኤስ ሞዴል ሱዙኪ ተሽከርካሪዎችን አላመርትም ያለው በቀይ ባህር ባለው ውጥረት ምክንያት ነው።
ኩባንያው ከቶኪዮ ሞተርና ሌሎች ግብአቶችን በፍጥነት ወደ ሃንጋሪ ማድረስ ባለመቻሉ ምርቱን ለማቋረጥ መገደዱን ነው ያስታወቀው።
በሰሜናዊ ሃንጋሪ ኢስዝቴርጎም በተባለችው ከተማ የሚገኘው የሱዚኪ ፋብሪካ ከስድስት ቀናት በኋላ ዳግም ወደ ምርት ይመለሳል ተብሏል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራቹ ቴስላም ባለፈው ሳምንት መሰል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ቴስላ ከበርሊን በቅርብ ርቀት የሚገኘው ፋብሪካው ግብአቶች በፍጥነት እየደረሱት አለመሆኑን በመጥቀስ ለሁለት ሳምንት ተሽከርካሪዎች ማምረት ማቆሙን ገልጿል።
የየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት የመርከቦችን እንቅስቃሴ እያወከ ነው።
ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ብቻ ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንደሚፈጽም ቢገልጽም ከቴል አቪቭ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው መርከቦችም ጭምር የጥቃቱ ኢላማ ሆነዋል በሚል ይከሰሳል።
አሜሪካም አጋሮቿን አስተባብራ የአለማችን ከ10 በመቶ በላይ ሸቀጦች የሚተላለፉበትን መስመር ከሃውቲ ጥቃቶች ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል።
አሜሪካ እና ብሪታንያ በየመን ከደርዘን በላይ የሃውቲ ወታደራዊ ይዞታዎችን መደብደባቸውን ተከትሎም ቡድኑ “ጠንካራና ውጤታማ” አጻፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ መዛቱ ይታወሳል።