የስዊድን ፖሊስ ቁርዓንና የኢራቅ ባንዲራን በህዝባዊ ስብሰባ ላይ ለማቃጠል ፈቃድ ሰጥቷል
በባግዳድ የሚገኘው የስዊድን ኤምባሲ ተወረረ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሀሙስ ማለዳ በኢራቅ ማዕከላዊ ባግዳድ የሚገኘውን የስዊድን ኤምባሲ ወረዋል።
የባግዳድ ኤምባሲ ሰራተኞች በሙሉ ደህና መሆናቸውን የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ፕሬስ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ቢሮው ጥቃቱን በማውገዝ፤ የኢራቅ ባለስልጣናት የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖችን የመጠበቅ አስፈላጊነት አመልክቷል።
የሀሙስ ሰልፉ የሺዓ መምህር በሆኑት ሙክታዳ ሳድር ደጋፊዎች የተጠራ ነው የተባለ ሲሆን፤ በሳምንታት ውስጥ በስዊድን ለሁለተኛ ጊዜ የታቀደውን ቁርዓን ማቃጠልን ለመቃወም ነው ተብሏል።
ከኢራቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዱ የሆኑት ሳድር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው አልፎ አልፎ ወደ ጎዳና እንዲወጡ ያዛሉ።
የስዊድን ፖሊስ እሮብ ዕለት በስቶክሆልም ከሚገኘው የኢራቅ ኤምባሲ ውጭ ለሚደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ሰጥቷል። ፖሊስ በስብሰባው ውስጥ ሁለት ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
የስዊድን የዜና ወኪል ቲቲ ሁለቱ ሰዎች ቁርዓን እና የኢራቅ ባንዲራን በህዝባዊ ስብሰባው ላይ ለማቃጠል ማቀዳቸውን ዘግቧል።
ከሁለቱ ሰዎች አንዱ በሰኔ ወር በስቶክሆልም ከመስጊድ ውጭ ቁርዓንን ያቃጠለው ሰው ነው ተብሏል።