ስዊድን ጦርነት ይከሰታል በሚል ለብዙ ሰዎች የቀብር ቦታ ማዘጋጀት ጀመረች
ኔቶን በቅርቡ የተቀላቀለችው ስዊድን በሩሲያ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት ውስጥ ነች
ሀገሪቱ ከጠቅላላ ህዝቧ ውስጥ አምስት በመቶው ሺህ ሊገደሉ ይችላሉ በሚል የቀብር ቦታ እያዘጋጀች ነው
ስዊድን ጦርነት ይከሰታል በሚል ለብዙ ሰዎች የቀብር ቦታ ማዘጋጀት ጀመረች።
አውሮፓዊቷ ስዊድን ሩሲያ ወደ ዩክሬን ጦሯን መላኳን ተከትሎ ነበር የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን የተቀላቀለችው።
በዓለም ጦርነት ወቅት በገለልተኛነቷ የምትታወቀው ስዊድን ኔቶን የተቀላቀለችው ሩሲያን በመስጋት ነበር።
አሁን ደግሞ ከሩሲያ ሊሰነዘር በሚችል ጥቃት ምክንያት ሰዎች በብዛት ሊሞቱ ይችላሉ በሚል የቀብር ቦታ ማዘጋጀት ጀምራለች ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
በስዊድን ካሉ ከተሞች መካከል በግዙፍነቱ ሁለተኛው የሆነው ጎትቦርግ ከተማ ብቻ በድንገት በሚከሰት ጦርነት ለሚሞቱ ሰዎች አራት ሄክታር መሬት ለቀብር አዘጋጅቷል።
የሀገሪቱ ከተሞች የቀብር ቦታ በስፋት ወደማፈላለግ የገቡት የስዊድን ጦር እና ሌሎች ተቋማት ጦርነት ሊኖር ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያ ካሰሙ በኋላ ነው።
ከአንድ ወር በፊት ሩሲያ ኦሬሽኒክ የተሰኘውን የኑክሌር ሚሳኤል ወደ ዩክሬን መተኮሷን ተከትሎ ስዊድን ዜጎቿን ከኑክሌር ጦርነት ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ማስተማር ጀምራ ነበር።
ከስዊድን በተጨማሪም ፊንላንድ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ ዜጎቻቸውን በጦርነት ወቅት እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ በማስተማር ላይ ናቸው።
ዴንማርክ እና ኖርዌይ ጦርነት ሊከሰት ይችላል ከሚል ስጋት ውጪ በሚያስተምሩት የቅድመ ጥንቃቄ ማስተማሪያ ይዘቶች ላይ የሩሲያን ስም አልጠቀሱም ተብሏል።
ሶስት ዓመት የሆነው የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ሲሆን ምዕራባውያን ለዩክሬን የረጅም ርቀት ጦር መሳሪያዎች በማስታጠቅ ላይ ናቸው።
ዩክሬን ከኔቶ አባል ሀገራት በምታገኛቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በሩሲያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ ናት።
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚሰጡ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎች ሶስተኛው የዓለም ጦርነትን ሊቀሰቅስ እንደሚችል በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች።