ፖለቲካ
አዲሷ የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር በተሾሙ በ7 ሰዓታት ውስጥ ስልጣን ለቀቁ
ሆኖም የፓርቲያቸው የ‘ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ አጣማሪ ‘ግሪን ፓርቲ’ ራሱን ከጥምረቱ ማግለሉን ተከትሎ በተሾሙ በሰዓታት ውስጥ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል
ማግዳሊና አንደርሰን ትናንት ረቡዕ ነበር የስዊድን የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሃገሪቱ ፓርላማ የተመረጡት
የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማግዳሊና አንደርሰን ስልጣን በያዙ በሰባት ሰዓት ውስጥ ለቀቁ፡፡
ስቴፋን ሎፍቬን ከሁለት ሳምንት በፊት ራሳቸውን ከሃላፊነት ማንሳታቸውን ተከትሎ የስዊድን እንደራሴዎች ምክር ቤት ማግዳሊና አንደርሰንን ትናንት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጦ ነበር፡፡
ማግዳሊና የመጀመሪያዋ ሴት የስዊድን ጠቅላይ ሚነስትርም ነበሩ፡፡
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሹመቱን ተቀብለው ስልጣን በያዙ በሰባት ሰዓት ውስጥ ስልጣናቸውን ለቀዋል፡፡
የ‘ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ መሪ የነበሩት አንደርሰን ስልጣናቸውን የለቀቁት በአገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አጣማሪያቸው የነበረው ‘ግሪን ፓርቲ’ ራሱን ከጥምረቱ ማግለሉን ተከትሎ ነው፡፡
‘ግሪን ፓርቲ’ ራሱን መንግስት ከመሰረተው የአንደርሰን ፓርቲ ጋር የመሰረተውን ጥምረት ያፈረሰው ምክር ቤቱ ያቀረበው የበጀት እቅድ መጽደቁን ተከትሎ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ስዊድንን ለሰባት ሰዓታት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አንደርሰን ራሳቸውን ከስልጣን ማግለላቸውን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡