የስዊድኗ ከተማ ነዋሪዎቿ ሰላምታ እንዲለዋወጡ አዲስ ዘመቻ ከፈተች
ነዋሪዎቼ ግለኝነታቸው አሳስቦኛል ብላ ዘመቻውን የጀመረችው ሉሊያ የተሰኘችው ከተማ ናት
ስዊድናውያን ማህበራዊ ግንኙነታቸው ቁጥብ ከሆኑ ህዝቦች መካከል ይጠቀሳሉ
ስዊድን በአይነቱ የተለየ ዘመቻ ጀምራለች፤ የሰላምታ ልውውጥ ዘመቻ።
ሉሊያ የተሰኘችው ከተማ ነዋሪዎች ያስጀመረችው አዲስ ዘመቻ በመላ ሀገሪቱ እንደሚስፋፋም ይጠበቃል።
ዘመቻውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ያስጀመሩት ሰዎች በፈገግታ ታጅበው ሰዎችን ሲጨብጡ የሚያሳዩ ምስሎችን ለቀዋል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ “ጎረቤታችንን ሰላም ማለት ቀላል ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ የማህበራዊ መስተጋብርን በእጅጉ ያጎለብታል” የሚል መልዕክትም አካቷል።
የሉሊያ ከተማ ነዋሪዎች በራሳቸው ግላዊ ህይወት ተጠምደው ለሌሎች ግድ የለሽ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል የዘመቻው አስተባባሪዎች።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጀመረው “ሰላም እንባባል” ዘመቻ በተለያዩ ግዙፍ ህንጻዎች እና አውቶብስ መጠበቂያ ስፍራዎች ላይ ለአንድ ወር ይቆያል ተብሏል።
በስዊድን በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እድሜያቸው ከ16 እስከ 29 የሚደርስ ወጣቶች ለብቸኝነት የተጋለጡ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ለዚህም የሀገሪቱ የአየር ንብረት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዘገበው።
በስዊድን በበጋ ወቅት ጸሃይ የምትወጣው በቀን ለሶስት ስአት ብቻ ነው፤ አማካይ የሙቀት መጠኑን ከ10 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሆነ ይነገራል።
ይህም ስዊድናውያን ከቤታቸው ወጥተው ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመገናኘት አዳጋች አድርጎባቸው በሂደት ማህበራዊ መስተጋብራቸው እየቀነሰ ሄዷል ተብሏል።