ሶሪያ ለጎረቤቶቿም ሆነ ለአለም ስጋት አይደለችም - አህመድ አል ሻራ
የሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን መሪው በበሽር አል አሳድ የስልጣን ዘመን በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ጠይቀዋል
በ2016 ከአልቃይዳ የተገነጠለውን ቡድን ሀገራት ከሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ እንዲያወጡት ጥሪ አቅርበዋል
በሶሪያ ስልጣን የያዘው ሃይል መሪ አህመድ አል ሻራ በጦርነት የተዳከመችው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ለጎረቤቶቿም ሆነ ለመላው አለም ስጋት አትሆንም አሉ።
የሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድንን ከሌሎች አማጺያን ጋር በማስተባበር ከሁለት ሳምንት በፊት ደማስቆን የተቆጣጠሩት አህመድ አል ሻራ ከቢቢሲ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል።
የ53 አመታት የአሳድ አገዛዝ አሁን አክትሞለታል ያሉት አል ሻራ፥ በቀደመው አስተዳደር ምክንያት በሶሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ጠይቀዋል።
"(በማዕቀቡ) ተጠቂዎች እና አምባገነኖች እኩል መታየት የለባቸውም" በማለትም ደማስቆ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በፍጥነት በማንሳት የወደመችውን ሀገር መልሶ የመገንባቱን ሂደት ማገዝ ይገባል ብለዋል።
አቡ ሞሀመድ አል ጆላኒ በሚል የትግል ስማቸው የሚታወቁትና ደማስቆን ከያዙ በኋላ ትክክለኛ ስማቸውን መጠቀም የጀመሩት አህመድ አል ሻራ፥ የሚመሩት ሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲሲ) ከሽብርተኛ ድርጅት ዝርዝር እንዲወጣም ነው የጠየቁት።
የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ሌሎች ሀገራትና አለማቀፍ ድርጅቶች በ2016 ከአልቃይዳ የተገነጠለውን ቡድን በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ይታወሳል።
ሻራ ግን ሃያት ታህሪር አል ሻም ሽብርተኛ ቡድን አይደለም ነው ያሉት። ቡድኑ ምንም እንኳን በአሳድ አገዛዝ የወንጀል ድርጊት ገፈት ቀማሽ ነኝ ብሎ ቢያምንም በንጹሃን እና በህዝባዊ አገልግሎት መስጫዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ጥቃት አለመፈጸሙንም ጠቅሰዋል።
መሪው ሶሪያን እንደ አፍጋኒስታን በአንድ ፈርጣማ ሃይል (ታሊባን) የምትመራ ሀገር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄም አስተባብለዋል።
"በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እስከ 60 በመቶ እንደሚደርስ እገምታለሁ" ያሉት አል ሻራ፥ ሴቶች መማር እንዳለባቸው አጥብቄ አምናለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።
የሶሪያ የህግ ባለሙያዎች ኮሚቴ አዲስ ህገመንግስት እንደሚያረቁና ውሳኔ እንደሚያሳልፉ በመጥቀስም "የትኛውም መሪ ወይም ፕሬዝዳንት ህጉን መከተል ይኖርበታል" ብለዋል።
በሶሪያ አሁን ላይ ትልቁ ስልጣን እንዳላቸው የሚታመነው አህመድ አል ሻራ በቃለምልልሱ ዘና ብለው ምላሽ ሲሰጡ ታይተዋል፤ የሚመሩት ቡድን ከቀደመ አክራሪ አቋሙ አልተላቀቀም ለሚሉ አካላትም ማረጋገጫ ለመስጠትም ሞክረዋል።
ሶሪያውያን ግን ስልጣን የጨበጡት ሃይሎችን ለማመን በቀጣይ ወራት የሚያሳልፏቸውን ውሳኔዎች ይጠብቃሉ።
ጎረቤት እስራኤልም የሶሪያ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች በአማጺያኑ እጅ ከገባ ከባድ ቀውስ ይፈጠራል በሚል ከጦርነት ነጻ በሆነው ክልል (በፈር ዞን) ጦሯን አስገብታ ዝግጅት ከጀመረች ሰነባብታለች።
የአሜሪካ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራት እና ቡድኖች የተለያየ ፍላጎትም ለ13 አመታት በእርስ በርስ ጦርነት አልፋ የበሽር አልአሳድ አገዛዝን የጣለችው ሶሪያ ቀጣይ እጣ ፈንታን የመወሰን ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው።