የሶሪያ አስተዳደር አዲስ የፖሊስ ሃይል ለማሰልጠን እስላማዊ አስተምህሮዎችን መጠቀም መጀመሩ ተነገረ
አስተዳደሩ የፖሊስ ምልምሎችን በስነምግባር ለማነጽ በማሰብ በስልጠናው ውስጥ ሀይማኖታዊ ትምህርትን ማካተቱን ገልጿል
የበሽር አላሳድ የጸጥታ ሀይሎች በሙስና እና ጭካኔያዊ ተግባር ይከሰሳሉ
የሶሪያ አስተዳደር አዲስ የፖሊስ ሃይሎችን ለማሰልጠን እስላማዊ አስተምህሮዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ጀመረ፡፡
አዲሱ መንግስት በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ለማግኘት እና የተረጋጋ ሰላም እና ጸጥታን ለማስፈን የጸጥታ ሀይሉን በማጠናከር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም በከተሞች የሚሰማሩ የፖሊስ አባላትን ለመመልመል እያደረገ በሚገኘው ጥረት በፖሊስ ስልጠና ውስጥ እስላማዊ አስተምህሮዎችን እየተገበረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች የፖሊስ ሀይልን ለመቀላቀል እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ከቀድሞ ጠንካራ የአማጺያን ይዞታ ምዕራብ ኢድሊብ የፖሊስ ሀይልን ለመቀላቀል የመጡ ዜጎች ሀይማኖታቸው እየተጠየቀ ምዝገባ እንደሚካሄድ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ ውሳኔ በበሽር አላሳድ መንግስት ወቅት በጭካኔ እና በሙስና የሚታወቁትን የጸጥታ ሀይሎች ስም ለመቀየር ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም አዳዲሶች የፖሊስ አባላት በስነምግባር እና የህዝብ አገልጋይነት እንዲታነጹ ሀይማኖታዊ አስተምህሮው ወሳኝ መሆኑን የሀገሪቱ ከፍተኛ የፖሊስ እና ጸጥታ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ ማካተት የሀይማኖታዊ ህጎች አተገባበር ስለሚኖረው ተጽዕኖ ገና የታወቀ ነገር ባይኖረውም በሂደቱ ዙሪያ ስጋቶች መደመጥ ጀምረዋል፡፡
የቀጠናው ተንታኞች በበኩላቸው ሀይማኖታዊ ትምህርትን በፖሊስ ስልጠና ውስጥ ማካተት የተለያዩ ሀይማኖቶች በሚገኙባት ሀገር አድልኦን እንዳያስከትል፤ እንዲሁም ምዕራባውያን ሀገራት የሀይማኖታዊ አስተዳደርን ለማስቀረት ከሚፈልጉት እቅድ ጋር እንዳይጋጭ ስጋት ፈጥሯል ይላሉ።
የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች አጥኚው አሮን ሉንድ ለሮይተርስ እንደተናገሩት አናሳ ቁጥር ያላቸው የክርስትና አምነት ተከታዮች እና የአላዋቲ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ ድሩዝ እንዲሁም በደማስቆ እና በአሌፖ በብዛት የሚገኙ የሱኒ ሙስሊሞች የሀይማኖታዊ ህግ መተግበርን አይፈልጉትም፡፡
የሶሪያው መሪ አህመድ አል ሻራ አስተዳደራቸው ከአልቃይዳ ጋር የነበረውን የቀድሞ ግንኙነት ማቋረጡን፤ አናሳ ቁጥር ያላቸው ሀይማኖቶችን እና ህዝቦችን ያማከለ መንግስት እንደሚመሰርቱ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል፡፡
የበሽር አላሳድ መንግስት መውደቅን ተከትሎ በአስተዳደሩ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ የጸጥታ ሀይሎች ተበትነዋል፡፡
አዲሱ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ 20 የሚሆኑ ፖሊስ ጣብያዎች ተከፍተዋል፤ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ከሚያስፈልጋቸው 150 የፖሊስ ሀይል ውስጥ ማግኘት የቻሉት 20 ፖሊሶችን ብቻ ነው፡፡