ሶሪያ ከዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ግብጽ ጋር ቀጣናዊ ውይይት ጀምራለች
ከዓመታት ጦርነት በኋላ በሽር አል አሳድ ወደ አረብ ሊግ አቅንተዋል።
የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በሳዑዲ አረቢያ በሚካሄደው የአረብ ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይገኛሉ ።
ይህም ከ350 ሽህ በላይ ሰዎች በተገደሉበት የእርስ በእርስ ጦርነት በአረብ መንግስታት የገጠማቸውን መገለል ይቋጫል ተብሏል።
ሶሪያ ሰኞ እለት የአረብ ሀገራት በጦርነት የምትታመሰውን ሀገር እንደገና ለመገንባት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቃለች።
የሶሪያ ይግባኝ የመጣው በሳዑዲ ከአረብ ሊግ ጉባኤ አስቀድሞ በተካሄደው የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ነው።
22 አባላት ያሉት የአረብ ሊግ ከ12 ዓመታት በኋላ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የሶሪያን አባልነት መልሷል።
ሊጉ የሶሪያውን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን ከረጅም ጊዜ መገለል በኋላ ወደ ህብረቱ ለማምጣት እርምጃ ወስዷል።
ሆኖም በአሳድ መንግስት ላይ የተጣሉ የምዕራባውያን ማዕቀቦች በነዳጅ የበለጸጉ የአረብ ሀገራት በሶሪያ ኢንቨስት ለማድረግ እንዳይቸኩሉ ሊያደርግ ይችላል ሲል ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።
አሊያም በጦርነት በተመታችው ሀገር ውስጥ የመልሶ ግንባታ ገንዘቡን በፍጥነት እንዲለቀቅ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።
ሶሪያ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ግብጽ ጋር ቀጣናዊ ውይይት ጀምራለች።
በኦማን የተጀመረው ንግግሩ የሶሪያን ግጭት ለመፍታት በአረቦች መሪነት የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል ነው ተብሏል።
የፊታችን አርብ በሚካሄደው የአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ ሶሪያ እንድትሳተፍ በይፋ ተጋብዛለች።