አሜሪካ በሶሪያ የአይ ኤስ ከፍተኛ አዛዥን መግደሏን ገለጸች
ካሊድ አይድ አህማድ አልጃቡሪ የተባለው የአይ ኤስ ከፍተኛ አዛዥ በአውሮፓ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን ሲያቀናባብር የቆየ ነው ተብሏል
አሜሪካ የአይ ኤስ መሪዎችን በአየር ጥቃቶች መግደሏ ቡድኑን ያዳክመዋል ቢባልም የአለም ሰላምና ደህንነት ስጋትነቱ አለመቀነሱን የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል
አሜሪካ በተናጠል በወሰደችው የአየር ጥቃት የአይ ኤስ ከፍተኛ አዛዥን መግደሏን አስታውቃለች።
በሶሪያ በተፈጸመው ጥቃት ካሊድ አይድ አህማድ አል ጃቡሪ የተባለው የቡድኑ አዛዥ ነው መገደሉ የተገለጸው።
በአየር ጥቃቱ በንጹሃን ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል የአሜሪካ ማዕከላዊ ማዛዣ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ።
አል ጃቡሪ በአውሮፓ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን በመምራት ተጠያቂ ስለመሆኑም መግለጫው አመላክቷል።
የግለሰቡ ግድያ የአይ ኤስን እንቅስቃሴ በተወሰነ መልኩ የሚያውክ ቢሆንም ቡድኑ አሁንም ለመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ብሎም ለመላው አለም ሰላምና ደህንነት አስጊ መሆኑም ተጠቅሷል።
በመሆኑም የቡድኑን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመግታት ዋሽንግተን አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዷን እንደምትቀጥል መግለጿንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
አሜሪካ ባለፈው ወርም ከሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር በመሆን በሄሊኮፕተር በፈጸመችው ጥቃት ሃምዛ አል ሃምሲ የተባለ የአይኤስ ከፍተኛ አመራርን መግደሏ የሚታወስ ነው።
በፈረንጆቹ 2014 አብዛኛውን የሶሪያ እና ኢራቅ ክፍል ተቆጣጥሮ የነበረው አይ ኤስ አይ ኤስ በሁለቱም ሀገራት ሽንፈት አስተናግዶ በአሁኑ ወቅት ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ አባላትና ደጋፊዎች በሀገራቱ እንዳሉት ይነገራል።
ይሁን እንጂ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በተለያዩ ሀገራት በቡድኑ ታጣቂዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች መጨመር ቡድኑ አሁንም ከፍ ያለ ስጋት መፍጠሩን ያሳያሉ።
አይ ኤስ ባለፈው አመት መሪው በደቡባዊ ሶሪያ ከተገደለ በኋላ አቡ አል ሁሴን አል ቁራይሺን መሾሙ ይታወሳል።