የሶሪያው መሪ በሽር አል-አሳድ በአረብ ኢሚሬስት ጉብኝት አደረጉ
ፕሬዝዳንት አሳድ ከ11 ዓመታት በኋላ ታካሪዊ የተባለውን ጉብኝት በአረብ ኢሚሬስት አድርገዋል
የአረብ ኢሚሬስት ለሽር አል-አሳድ ያደረገችው አቀባበል አሜሪካን አበሳጭቷል
የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ በሀገራቸው ጦርነት ከተጀመረ ከ11 ዓመታ በኋላ በአረብ ሀገራት ታሪካዊ የተባለውን ጉብኘት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አካሄዱ።
ፕሬዝዳንት በሽር አል-አሳድ በትናትናው እለት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የገቡ ሲሆን፤ በቆይታቸውም ከበርካታ ተጽእኖ ፈጣሪ የሀገሪቱ መሪዎች ጋር ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልበት ላይ መክረዋል።
አሳድ በዱባይ ቆይታቸው ከዱባዩ ገዢ ቢሊየነር ሼክ መሃመድ አል መክቱምን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ወደ አቡ ድሃቢ በማቅናትም ከልኡል አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አለ ናህናያን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ሶሪያ ለአረብ ሀገራት ደህንነት ወሳኝ አጋር እንደሆነች ያነሱት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከሶሪያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።
መሪዎቹ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሶሪያ ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ በምትችልበትን መንገድ እንዲሁም በህዝቦች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ንግድ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
የሶሪያ ፕሬዝዳንት በሽር እለ-አሳድ በሀገራቸው ከ350 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት በፈረንጆቹ 2011 ከጀመረ ወዲህ ጥቂት አለም አቀፍ ጉዞዎችን ብቻ ማድረጋቸው ይነገራል።
አል-አሳድ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ እስካሁን ወታደራዊ ድጋፎችን በሚያደርጉላቸው ሩሲያ እና ኢራን ብቻ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ አረብ ኢሚሬትስ ሶስተኛ ሀገራቸው ነው።
ጉብኝቱን ተከትሎ የአሜሪካ ባወጣችው መግለጫ፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሶሪያውን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን መቀበሏ “በጣም እንዳበሳጫትን እና እንዳስጨነቃት” አስታውቃለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "ከአሳድ መንግስት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስቡ ሀገራት ገዥው አካል ባለፉት አስር ዓመታት በሶሪያውያን ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ግፍ ባገናዘበ መልኩ እንዲሆን እናሳስባለን” ብለዋል።
በሶሪያ በፈረንጆቹ 2011 የተቀሰቀሰውን የእርስ በእስር ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ከአብዛኞቹ የአረብ ሀገራት ጋር በመሆን ከሶሪያ ጋር የነበራትን ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ከዋሽንግተን ተቃውሞ ቢያጋጥማትም ሶሪያን ወደ አረብ ሀገራ ጎራ ለመመለስ ጥረቷን ቀጥላለች።
አረብ ኢሚሬትስ በሶሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን በፈረንጆቹ 2018 መልሳ የከፈተች ሲሆን፤ ባሳለፍነው ዓመትም ከፍተኛ የአረብ ኢሚሬትስ ዲፕሎማቶች ከፕሬዝዳንት አሳድ ጋር ለመምከር ወደ ሶሪያ ማቅናታቸው ይታወሳል።