የሶሪያ የሽግግር ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ ሳኡዲ ገቡ
የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በሪያድ እያደረጉ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር ይመክራሉ

ሪያድ በደማስቆ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች
የሶሪያው የሽግግር ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በሳኡዲ አረቢያ እያደረጉ ነው።
አል ሻራ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳድ አል ሻባኒ ጋር በሳኡዲ ጄት ሪያድ የገቡ ሲሆን ከልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር እንደሚመክሩ ዘጋርዲያን አስነብቧል።
ባለፈው ሳምንት ህገመንግስቱን ሽረው፤ ፓርላማ በትነው የሽግግር መንግስት ያቋቋሙት በሽር አል አሳድን ከስልጣን ያነሱት ወታደራዊ መሪዎች አል ሻራ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መርጠዋቸዋል።
ጊዜያዊ መሪው የአሳድ ደጋፊ ከነበረችው ኢራን ይልቅ ከሳኡዲ ጋር ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው።
ኢራን በደማስቆ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዳግም ለመክፈት እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፥ ሌላኛዋ የአሳድ ደጋፊ የነበረችው ሩሲያም በሶሪያ የሚገኘው የአየር እና ባህር ሃይል ማዘዣ ጣቢያዋ ስራውን እንዲቀጥል ትፈልጋለች።
በታህሳስ ወር የበሽር አል አሳድ አገዛዝን ያስወገደው ሃያት ታህሪር አል ሻም መሪው አህመድ አል ሻራ ግን ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነታቸውን ለማስተካከል ከሳኡዲ አረቢያ ጋር መተባበርን መርጠዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳድ አል ሻባኒ የተመራ ልኡክ ባለፈው ወር በሪያድ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።
የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልኡል ፈይሰል ቢን ፋርሃትም በጥር ወር በደማስቆ ባደረጉት ጉብኝት ሪያድ በአሳድ አገዛዝ ወቅት በደማስቆ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ በሚደረጉ ድርድሮች "በንቃት እየተሳተፈች ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።
ኳታርም እንደ ሳኡዲ ሁሉ በሶሪያ አሳድን አስወግዶ ስልጣን የያዘው ሃይል በ13 አመት የእርስ በርስ ጦርነት የፈራረሰችውን ሀገር ዳግም ለመገንባት የገባው ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን እደግፋለሁ ብላለች።
የሽግግር መንግስቱ እንደ አይኤስአይኤስ ካሉ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ስጋት ደቅነውበታል።
በትናንትናው እለት በማንጂብ ከተማ በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ የአራት ንጹሃንን ህይወት ቀጥፎ ዘጠኝ ሰዎች መጎዳታቸውን ሳና የተሰኘው የሀገሪቱ የዜና ወኪል ዘግቧል።