ሶሪያ ላለፉት 10 ዓመታት በእር በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየች ሲሆን፣ ከ400 ሺህ በላይ ዜጎቿ በጦርነቱ ሞተዋል
በእርስ በእስር ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሶሪያ በቀጣዩ ግንቦት ወር ላይ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ የሀገሪቱ ፓርላማ አስታወቀ።
የሀገሪቱ ፓርላማ ውሳኔም ፕሬዚደንት በሽር አላሳድን በስልጣን ላይ ለማቆየት ያለመ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ለቀጣይ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራውን ፕሬዚደንት ለመምረጥ የሚካሄደው ምርጫ በአውሮፓውያኑ የፊታችን ግንቦት 26/2021 እንደሚካሄድ የሀገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሀሙዳ ሳባግህ አስታውቀዋል።
ከነገ ሰኞ ጀምሮ በምርጫው ላይ እጩ ሆነው መቅረብ የሚፈልጉ አካላት ምዝገባ እንደሚጀመር ያስታወቁት አፈ ጉባዔው፤ ከሀገሪቱ ውጭ የሚገኙ ሶሪያውያን በሀገሪቱ ኤምባሲዎች ተገኝተው ድምጽ የሚሰጡ ይሆናልም ብለዋል።
ለ20 ዓመታት ሶሪያን በፕሬዚደንትነት የመሩት በሽር አላሳድ በአሁኑ ምርጫ ብርቱ ተፎካካሪ ይገጥማቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።
ሶሪያ ላለፉት 10 ዓመታት በእር በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየች ሲሆን፤ የፊታችን ግንቦት ወር የሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም የእር በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው።
የመጀመሪያው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በፈረንጆቹ 2014 የተካሄደ ሲሆን፤ በሽር አላሳድ 92 በመቶ ድምጽ በማግኘት ምርጨውን ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
እስካሁን መቋጫ ያልተገኘለት የሶሪያ የእር በእርስ ጦርነት ከ400 ሺህ በላይ ሶሪያውያንን ህይወት ቀጥፏል።
በተጨማሪም የእር በእርስ ጦርነቱን በመሸሽ በርካታ ሶሪያውያን ሀገራቸውን ጥለው ለስደት መዳረጋቸውም ይታወቃል፡፡