ሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት አንድ ዶላር በ47 የሶሪያ ፓውንድ ይመነዘር ነበር
ሶሪያ የገንዘቧን የመግዛት አቅም ይበልጥ ማዳከሟ ተነገረ።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ4 ሺህ 522 የሶሪያ ፓውንድ እንዲመነዘር መወሰኑን ይፋ አድርጓል።
ከትናንቱ ውሳኔ በፊት አንድ ዶላር በ3 ሺ 15 የሶሪያ ፓውንድ ሲመነዘር መቆየቱ ነው የተገለጸው።በጥቁር ገበያው ግን አንድ ዶላር እስከ 6 ሺህ 500 የሶሪያ ፓውንድ እንደሚመነዘር ሮይተርስ ዘግቧል።
በጦርነት የደቀቀው የሶሪያ ኢኮኖሚ ጎረቤቷ ሊባኖስ የገጠማት ቀውስ እና ደቡብ ምስራቃዊ የሶሪያ የነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎች በታጣቂዎች መያዝ የገንዛቧን የመግዛት አቅም ይበልጥ እንድታዳክም አድርጓታል።
ይህም ሶሪያውያን ለምግብ፣ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች የሚያወጡትን ወጪ እጅግ እንደሚያንረው ነው የሚጠበቀው።
ኤሌክትሪክ በፈረቃ እያቀረበ ያለው የበሽር አል አሳድ መንግስት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የህዝብ መገልገያ ተቋማትን እስከመዝጋት የደረሰ የሃይል አቅርቦት ፈተና ገጥሞታል።
በፈረንጆቹ መጋቢት ወር 2011 በበሽር አል አሳድ ላይ ተቃውሞ ከመነሳቱ በፊት በሶሪያ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ47 የሶሪያ ፓውንድ ይመነዘር ነበር።ትናንት በተደረገው ማሻሻያ ግን የአንድ ዶላር ዋጋ ወደ 4 ሺ 522 የሶሪያ ፓውንድ ከፍ ብሏል።
ይህም በጦርነትና በምዕራባውያን ማዕቀብ የደቀቀውን የደማስቆ ምጣኔ ሃብት ይበልጥ ቀውስ ውስጥ ይከተዋል ነው የተባለው።