የአረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አመላካች አሃዞች
የኤምሬትስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ እና የአቡ ዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታኑን ቢን ዛይድ ከዛሬ ጀምሮ በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ

የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል
አረብ ኤምሬትስ ከአሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው እንደ ሀገር በተመሰረተች (በፈረንጆቹ 1971) ማግስት ነው።
በዋሽንግተን የሚገኘው የኤምሬትስ ኤምባሲ በይፋ የተመረቀው በ1974 ሲሆን፥ አሜሪካም በተመሳሳይ አመት በአቡዳቢ ኤምባሲዋን ከፍታለች።
የ50 አመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር ፈጥረዋል።
የኤምሬትስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ እና የአቡ ዳቢ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ ታኑን ቢን ዛይድ አል ናህያንም ይህንኑ ግንኙነት ለማጠናከር ከዛሬ ጀምሮ በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ።
የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም እንዳስነበበው ታኑን ቢን ዛይድ አል ናህያን በዋሽንግተን ቆይታቸው ከሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ባሻገር በቀጠናዊ ጉዳዮችም ይመክራሉ።
ኤምሬትስ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል የአሜሪካ የወጪ ንግድ ቀዳሚ መዳረሻ ሀገር ናት።
አቡ ዳቢ ከ2018 እስከ 2023 ድረስ በአማካይ የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ ንዋይ በአሜሪካ ላይ አፍስሳለች። በአጠቃላይ ኤምሬትስ በአሜሪካ ኢንቨስት ያደረገችው 35 ቢሊየን ደርሷል።
በአንጻሩ አሜሪካ በ2022 መጨረሻ በኤምሬትስ 5 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ማድረጓን የዋም መረጃ ያሳያል።
ከ1500 በላይ የዋሽንግተን ኩባንያዎች በአቡ ዳቢ በኢነርጂ፣ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ገበያ ዘርፎች ኢንቨስት አድርገዋል።
የኤምሬትስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ የአሜሪካ ጉብኝት ከ2019 ወዲህ በ46 በመቶ ያደገውን የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።