በፈጣን ግስጋሴ ላይ የሚገኘው የኤምሬትስና አሜሪካ የንግድ ግንኙነት
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የመጀመሪያውን የአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ዛሬ ዋሽንግተን ይገባሉ
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በ2023 31.4 ቢሊየን ዶላር ደርሷል
የ50 አመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን እያጠናከሩ ነው።
የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በዋይትሃውስ ከአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢኮኖሚና ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የታዳሽ ሃይል ልማት፣ የህዋ ምርምርና ቴክኖሎጂ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ይሆናሉ ተብሏል።
ኤምሬትስ ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል የአሜሪካ የወጪ ንግድ ቀዳሚ መዳረሻ ሀገር ናት።
የኤምሬትስ እና አሜሪካ የንግድ ልውውጥ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2023 31.4 ቢሊየን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
አሜሪካ በ2023 ወደ ኤምሬትስ የላከችው ምርትና አገልግሎት 24.8 ቢሊየን ዶላር መድረሱን በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኤምሬትስ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
ኤምሬትስ በአሜሪካ በሪል ስቴት፣ ታዳሽ ሃይል ልማት እና ሌሎች ዘርፎች ያፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ 1 ትሪሊየን ዶላር መድረሱም ነው የተጠቀሰው።
ዋሽንግተንም በኤምሬትስ በኢነርጂ፣ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ገበያ የተሰማራች ሲሆን፥ ከ1500 በላይ ኩባንያዎቿ በአቡ ዳቢ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት አድርገዋል።
ኤምሬትስ ሁለተኛ ሀገራቸው ያደረጉ ከ50 ሺህ በላይ አሜሪካውያንም የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር በማሳደግ ላይ ይገኛሉ።
የዋሽንግተን እና አቡ ዳቢ የንግድ ትስስር ለ166 ሺህ አሜሪካውያን የስራ እድል መፍጠሩም ነው የተነገረው።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታም ከ31 ቢሊየን ዶላር በላይ የደረሰውን የሀገራቱን የንግግድ ልውውጥና ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።