የ”ዶንባስን እጣ ፈንታ” ይወስናል የተባለው ጦርነት በዩክሬኗ ሰቨሮዶነስክ ከተማ እየተካሄደ ነው -ዘለንስኪ
በሰቨሮዶነስክ ከተማ እየተካሄደ ያለውን ከባድ ጦርነት ተከትሎ የዩክሬን ኃይሎች ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ነው ተብሏል
በሰቨሮዶነስክ 15 ሺህ ሲቪል ሰዎች እንዳሉ መረጃወች ይጠቁማሉ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ የዶንባስን እጣ ፈንታ ይወስናል ያሉት ጦርነት በዩክሬኗ ሰቨሮዶነስክ ከተማ እየተካሄደ ነው አሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደሆነ በሚነገርለት የዩክሬን ምስራቃዊ ክፍል ፤ የዩክሬን ኃይሎች ከሩሲያና ተገንጣይ አጋሮቻቸው ጋር ከባድ ፍልሚያ እያካሄዱ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ የዶንባስን እጣ ፈንታ በዚህ ጦርነት የሚወሰን ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዘሌንስኪ፤ የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ኃይሎች ላይ ከባድ ወታደራዊ ኪሳራ እያደረሱ መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጅ የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ኃይሎች ተገፍተው ከተማዋ ለቀው ለመውጣት እየተገደዱ እንደሆን ፍራንስ-24 ዘግቧል፡፡
የሉሃንስክ ግዛት አስተዳዳሪ ሰርሂ ሀዳይ በበኩላቸው፤ የሩሲያ ኃይሎች በአውሮፕላን እና ከባድ መሳሪያዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘራቸውንና የከባድ ብረት ድብደባ ማካሄዳቸው ተከትሎ የዩክሬን ኃይሎች ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው አስታውቋል፡፡
“እርግጥ ነው አሁን ላይ ሰራዊታችን የተቆጣጠረው የከተማዋ ዳርቻዎች ብቻ ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ አሁን ላይ ጦርነቱ 15 ሺህ ሲቪል ሰዎች እንዳሉዋት በሚነገርላት ሰቨሮዶነስክ ከተማ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በትናንትናው እለት ፤ ዩክሬን ዶንባስ ላይ “ ከባድ ወታደራዊ ኪሳራ በማስተናገድ ላይ ናት” ማለቷ አይዘነጋም፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ መጋቢት ኪቭን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረገችው ሩሲያ፤ በወቅቱ ከዩክሬን ኃይሎች የገጠማትን ከፍተኛ ወታደራዊ አጸፋ ተከትሎ አቅጣጫ በመቀየር ምስራቅ ዩክሬንን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በተለያዩ ምክንያቶች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡
የዓለም ባንክ በትናንትናው እለት ባወጣው ሪፖርት፤ የዩክሬን ጦርነት ቀድሞውንም የተናወጠውና በኮቪድ ወረርሺኝ የተመታው የዓለም ኢኮኖሚ፤ ውድቀት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
“የኢኮኖሚ ውድቀቱ” በተለይም በደምብ ባላደጉ የአውሮፓና ምስራቅ እስያ ሀገራት የከፋ እንደሆነም ተቋሙ ገልጿል፡፡
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ መልፓስ፡ ‘ስታግፍሌሽን’ ተብሎ የሚታወቀው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መኖርና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንዳለም ነው የተናገሩት ተናግረዋል፡፡
ዴቪድ መልፓስ “የዩክሬን ጦርነት፣ በቻይና ያለው ተጽእኖ (ኮቪድ-19)፣ የአቅርቦት መቆራረጥ፣ በጥሬ እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት የዓለም ኢኮኖሚ እያዳከሙት ነው፣ በዚህም በብዙ ሀገራት የኢኮኖሚ ውድቀት ማጋጠሙ አይቀሬ ነው ”ም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም አውሮፓ ህብረት ፡ ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንደ ‘ድብቅ ሚሳኤል’ እየተጠቀመችበት ነው ሲል የከሰሰው ከቀናት በፊት ነበር፡፡
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱት ቻርለስ ሚሸል፤ ሩሲያ የምግብ አቅርቦትን እንድ ድብቅ ሚሳዔል በመጠቀም በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ለከፋ ድህነት እየዳረገች ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሚሸል ከቀናት በፊት በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፤ “የሚያሳዝነው ሩሲያ የጀመረችው ጦርነት በመላው ዓለም እየተዛመተ መሆኑ ነው፤ የምግብ ዋጋ እጅጉን እንዲንር በማድረግ የዓለም ህዝቦች ለድህነት እንዲዳረጉና የተለያዩ ቀጠናዎች እንዲታመሱ እያደረገ ነው ፤ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ ሩሲያ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡