ታይዋን የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና የአሜሪካን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተቃውማለች
የታይዋን ጦር ከአሜሪካ 619 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለማግኘት መቃረቡ ተነግሯል።
የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን ሰርጥ ለሁለት ተከታታይ ቀናት መብረራቸው በተገለጸ ማግስት ነው ፔንታጎን ለታይፒ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መወሰኑን ያስታወቀው።
በሽያጭ ውሉ ከ200 በላይ ጸረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች መካተታቸውም ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያጸደቀው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል፥ የደሴቷን የአየር ጥቃት የመከላከል አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድገው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፥ “ከአሜሪካ የምናገኛቸው ሚሳኤሎች የቤጂንግን ጸብ አጫሪ ድርጊቶች ለመመከት ያግዙናል” ብሏል።
ሚሳኤሎቹን ራይተን ቴክኖሎጂስ እና ሎክሄድ ማርቲን የተሰኙ የአሜሪካ ኩባንያዎች ያቀርባሉ ተብሏል።
እነዚህ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደምም ለታይዋን የጦር መሳሪያ በመሸጣቸው በቻይና ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ሬውተርስ አስታውሷል።
ቻይና ፔንታጎን ትናንት ይፋ ያደረገውን የ619 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውልም ተቃውማዋለች።
ቤጂንግ የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትላት ታይፒ እንደ ሉአላዊ ሀገር ከሌሎች ሀገራት ጋር መሰል ስምምነት መፈራረም እንደማትችል ደጋግማ ማሳሰቧ ይታወሳል።
ታይፒ ግን ባለፉት ሶስት አመታት በተለይ ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነቷን አጥብቃ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቶችንም ፈጽማለች።
ይህ በጦር መሳሪያ ሽያጭ የሚታይ የዋሽንግተን ጣልቃገብነት የቤጂንግን ወታደራዊ ዝግጁነት እያጠናከረው ስለመምጣቱም ነው የሚነገረው።
በየእለቱ በታይዋን ሰርጥ አካባቢ ቅኝት የሚያደርጉ የቻይና አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መሄዱም ውጥረቱን አንሮታል።