ታይዋን በ25 አመታት ውስጥ ከባድ በተባለ የርዕደ መሬት አደጋ ተመታች
ጃፓን እና ፊሊፊንስም የማዕበል ማስጠንቀቂያ አውጥተው ነበር
የታይዋን መንግስት የርዕደ መሬት አደጋው መነሻ በሆነች ተራራማዋ የሁዋሌን ግዛት አራት ሰዎች መምታቸውን እና 50 ሰዎች መጎዳታቸውን አስታውቋል
ታይዋን ቢያንስ በ25 አመታት ውስጥ መጠኑ በሬክተርስኬል 7.2 በሆነ ከባድ የርዕደ መሬት አደጋ መመታቷ ተገለጸ
ይህ የርዕደ መሬት አደጋ በደቡባዊ ጃፓን እና ፊሊፊንስ የሱናሜ(ማዕበል) ማስጠንቀቂያ እንዲወጣ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የታይዋን መንግስት የርዕደ መሬት አደጋው መነሻ በሆነችው ሰዎች ተበታትነው በሚኖሩባት ተራራማዋ የሁዋሌን ግዛት አራት ሰዎች መምታቸውን እና 50 ሰዎች መጎዳታቸውን አስታውቋል።
በዚህ አደጋ ቢያንስ 26 ህንጻዎች የተደረመሱ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሁዋሌን ግዛት የሚገኙ ናቸው።
የታይዋን ቴሌቪዥን በርዕደ መሬት አደጋው የተጣመሙ እና ያዘነበሉ ህንጻዎችን የሚያሳይ ቪዲዮ አሳይቷል።
እንደታይዋን ሴንትራል ዌዘር አድሚኒስትሬሽን ከሆነ ርዕደ መሬቱ 15.5 ኪሎሜትር ጥልቀት አለው።
በአሁኑ ወቅት የነፍስ አድን ሰራተኞች መሰላል በመጠቀም በአደጋው ከአዘነበሉ ህንጻዎች ሰዎችን እያወጡ ሲሆን በሌላ ቦታ ደግሞ ርዕደ መሬቱ ባስከተለው ንዝረት የመሬት መንሸራተት ተከተስቷል።
የጃፓን ዌዘር አጄንሲ እንደገለጸው በኦኪናዋ ደቡባዊ ክፍል በርካታ ሱናሜዎች ተከስተው የነበረ ቢሆንም ቆይተው ሸሽተዋል።
የፊሊፊንስ ሴስሞሎጂ ኤጀንሲም በበርካታ የጠረፍ ግዛቶች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ከፍታ ቦታ እንዲወጡ አስጠንቅቆ ነበር።