ፖለቲካ
በታይዋን በደረሰ የባቡር አደጋ በትንሹ 36 ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም ተባለ
የአደጋው መንስዔ አንድ በአግባቡ ቆሞ ያልነበረ ተሽከርካሪ ስለመሆኑም ተነግሯል
አደጋው 350 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የመንገደኞች ባቡር ሃዲዱን ስቶ በመጋጨቱ ያጋጠመ ነው ተብሏል
ዛሬ ጠዋት በምስራቃዊ ታይዋን ሲጓዝ የነበረበትን ሃዲድ ስቶ በተጋጨ ባቡር በደረሰ አደጋ በትንሹ 36 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ፡፡
አደጋው 350 ሰዎችን አሳፍሮ ‘ኒው ታይፒ’ ተብላ ከምትጠራው ሹሊን ተነስቶ ታይቱንግ ወደ ተሰኘች ከተማ ሲያመራ የነበረ ባለ 8 ፍርጎ ባቡር ‘ዳቂንግሹይ’ ከተባለ ዋሻ ውስጥ ሲገባ ሃዲዱን በመሳቱ ያጋጠመ ነው፡፡
እንደ ሃገሪቱ ባቡር መንገዶች አስተዳደር ባለስልጣን ገለጻ የባቡሩን ሹፌር ጨምሮ የ36 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ አልፏል ፡፡
ሌሎች 61 ተሳፋሪዎች ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ሌሎች 72 የባቡሩ ተሳፋሪዎች ደግሞ በዚያው በዋሻው ውስጥ ይገኛሉ፡፡
እንደ ባለስልጣኑ ገለጻ ከሆነ የአደጋው መንስዔ አንድ በአግባቡ ቆሞ ያልነበረ ተሽከርካሪ ነው፡፡
ተሽከርካሪው በአካባቢው በሚገነባ አውራ መንገድ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአግባቡ እንዲቆም ባለመደረጉ ምክንያት ወደ ኋላ ተሽከርክሮ ከባቡሩ ጋር ሊጋጭና ባቡሩን ከሃዲዱ ሊያስወጣው ችሏል፡፡
የግንባታው ሰራተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በመመርመር ላይ ናቸው እንደ ታይዋን ኒውስ ዘገባ፡፡