ታሊባን፤ ፓኪስታን የአልቃዒዳው መሪ አል-ዛዋሂሪ እንዲገደል ለአሜሪካ የአየር ክልሏን ፈቅዳለች ሲል ከሰሰ
የታሊባን መከላከያ ሚኒስቴር፤ “ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ አፍጋኒስታን የሚገቡት በፓኪስታን በኩል እንደሆነ መረጃ አለን” ብሏል
ታሊባን ይህን ቢልም ግን፤ በፓኪስታን በኩል ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የተባለ ነገር የለም
ታሊባን፤ ፓኪስታን የአልቃዒዳው መሪ አል-ዛዋሂሪ እንዲገደል “የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ አየር ክልሏ እንዲገቡ ፈቅዳለች” ሲል ከሰሰ፡፡
የታሊባን ተጠባባቂ የመከላከያ ሚኒስትር ሙላህ መሀመድ ያቁብ በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በፓኪስታን በኩል ወደ አፍጋኒስታን ገብተው በካቡል ጥቃት ሊፈጽሙ መቻላቸው ተናግረዋል።
"በእኛ መረጃ መሰረት ድሮኖች በፓኪስታን በኩል ወደ አፍጋኒስታን ይገባሉ፤ ለዚህም የፓኪስታንን የአየር ክልል ይጠቀማሉ፤ እናም እኛ ፓኪስታንን የአየር ክልሏ እኛን በሚጻረር መልኩ አትጠቀሚበት ስንል እንጠይቃለን "ም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
ታሊባን ይህን ቢልም ግን፤ በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የተባለ ነገር አለመኖሩ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአልቃዒዳውን መሪ አይመን አል-ዛዋሂሪ ሃምሌ 30 ቀን 2022 እቤቱ በር ላይ ተቀምጦ በነበረበት ከአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች እንደተገደለ የሚታወስ ነው፡፡
አል-ዛዋሃሪ ከቀድሞው የአልቃኢዳ መሪ ቢንላደን ጋር በመሆን የ 9/11 ጥቃትን የመራ ሲሆን አሜሪካ ለረጅም አመታት ስታፈላልገው የቆየች የሽብር ቡድኑ መሪ ነበር።
የኦሳማ ቢንላደን ህልፈትን ተከትሎም አል-ቃዒዳን ሲመራ ቆይቷል።
አል-ዛዋሂሪ እንደፈረንጆቹ በጥቅምት 2000 በኤደን የአሜሪካ የባህርኃይል አውዳሚ ላይ በተሰነዘረ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 17 የአሜሪካ መርከበኞችን የገደለውን ጥቃት እንደመራም ይነገርለታል፡፡
በተጨማሪም፤ ለ223 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆኑት በ1998 በኬንያ እና ታንዛኒያ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በማስተባበር አል- ዛዋሂሪ ሃላፊነት እንዳለበት ይነሳል።