የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በታሊባን ባለስልጣናት የጉዞ እገዳ ጉዳይ ተከፋፍለዋል ተባለ
ከፊል የምክር ቤቱ አባላት በባለስልጣናቱ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ መነሳቱን ተቃውመዋል
ምክር ቤቱ በ2011 በ135 የታሊባን አመራሮች ላይ የጉዞ እና የሃብት እገዳን ጥሎ ነበር
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በታሊባን ከፍተኛ አመራሮች የጉዞ እገዳ ጉዳይ መከፋፈላቸው ተነገረ።
አየርላንድን መሰል የምክር ቤቱ አባላት በተወሰኑ የቡድኑ አመራሮች ላይ የተጣለውን እገዳ ልክ ከአሁን ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ ለማደስ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
ምክር ቤቱ በ2011 ውሳኔው በ135 የታሊባን አመራሮች ላይ የጉዞ እና የሃብት እገዳን ጥሎ ነበር።
ሆኖም 13ቱ እገዳው በተለያየ ጊዜ እየተነሳላቸው አንዳንዴም በየወሩ እየታደሰ ወደ ተለያዩ ሃገራት ሲጓዙና ግንኙነቶችን ሲያደርጉ ነበር።
ነገር ግን የእገዳው የማሳደሻ ጊዜ ባሳለፍነው አርብ ተጠናቋል። የምክርቤቱ ተለዋጭ አባል የሆነችው አየርላንድ ባቀረበችው ተቃውሞ ምክንያትም ሳይታደስ ቀርቷልም ነው የተባለው።
በዚህም ድምጽን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸውን ቋሚዎቹን የምክር ቤቱን አባላት ጨምሮ በጉዳዩ ላይ መስማማት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የአፍጋኒስታንን ጉዳይ የሚከታተለውና 15 አባላት ያሉት የምክር ቤቱ ኮሚቴ ሴቶች እንዳይማሩ ከልክለዋል በሚል እገዳው ሲታደስላቸው በነበሩ ሁለት የቡድኑ አባላት ላይ የጣለውን እገዳ አጽንቶ ነበር።
ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ ሲቆጣጠር መብቶችን ለማክበርና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የገባውን ቃል እያከበረ አይደለም በሚል የሚከሱት አሜሪካ እና ምዕራባዊ አጋሮቿም ይህ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ።
ሆኖም ቻይና እና ሩሲያ የእገዳውን እንደተለመደው ሁሉ አለመታደስ ተቃውመዋል። ጉዞውን እና ሌሎች ጉዳዮችን ማያያዙ እንደማይጠቅም የተናገሩት የቻይና ተወካይም እደሳው እንደሚጠቅም ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ መነጋገሩ እንደሚቀጥልም ነው የተገለጸው።
አሜሪካ የአል ቃይዳ መሪ እንደሆነ የሚነገርለትን ግብጻዊውን አይማን አል ዘዋሂሪን በአፍጋኒስታን ገደልኩት ስትል ከወር በፊት ማስታወቋ የሚታወስ ነው።