ታሊባን ዳኞች በጥፋተኞች ላይ የአደባባይ ግድያ፣ በድንጋይ እና በግርፋት መግደልና መሰል ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ አዟል
ታሊባን የግድያ ወንጀል ፈጽሟል ያለውን አፍጋኒስታናዊ በአደባባይ መግደሉ ተገለጸ።
የግድያ እርምጃው የአሜሪካና አጋሮቿ ጦር ከአፍጋኒስታን መልቀቁን ተከትሎ ዳግም ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ በሰጡት መግለጫ የቅጣት ውሳኔው አፍጋኒስታናውያን በተሰበሰቡበት ወቅት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
የተገደለውን ግለሰብ ታጅሚር በመባል የሚታወቅ የአንጂል ወረዳ ነዋሪ እንደሆነም ገልጸዋል ቃል አቀባዩ፡፡
የታሊባን የበላይ መሪ ሂባቱላህ አኩንዝዳዳ ዳኞች በጥፋተኞችና ሌቦች ላይ የአደባባይ ግድያ፣ በድንጋይ እና በግርፋት እንዲሁም እጅና እግር መቁረጥን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችን እንዲያስፈጽሙ ማዘዛቸው ባላፈው ወር ትእዛዝ ማስተላለፈቻው አይዘነጋም።
የሂባቱላህ አኩንዝዳዳን ትእዛዝ ተከትሎ ብዙ የአደባባይ ግርፋቶች የተፈጸሙ ቢሆንም ረቡዕ ፋራህ በተባለ አፍጋናዊ የተፈጸመው የአደባባይ ግድያ የመጀመሪያ ነው ተብሏል፡፡
ታሊባን በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ አፍጋኒስታንን ሲምራ በራሱ ፍርድ ቤቶች ወንጀለኛ ናቸው ያላቸውን ሰዎች በአደባባይ ሲግድል፣ ሲገርፍ እና በድንጋይ ሲወግር እንደነበር የሚታወስ ነው።
ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በ2021 እንደገና ወደ ስልጣን የተመለሰው ታሊባን ቀደም ሲል ሲደፈጥጣቸው የነበሩ መብቶችን ያከብራል ተብሎ ቢጠበቅም አሁንም ምንም አይነት ለውጥ አለማድረጉ እያነጋገረ ነው፡፡
በተለይም የሴቶችን እና የአናሳ ቡድኖችን መብት ለማክበር የገባውን ቃል አለማክበሩ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ተቃውሞ እንዲገጥመው አድርጓል።
ታሊባን በአፍጋኒስታን ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ያለው አያያዝ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ያመለክታል፡፡
የተመድ ሪፖርት ይህን ያመላክት እንጅ የካቡል ባለስልጣናት ግን ክሱን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አብዱል ቃሃር ባልኪ “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶች መብት እና እኩልነት ስም በሚጥለው ማዕቀብ ንጹሃን አፍጋኒስታናውያንን እየቀጣ ነው” ሲሉ በቅርቡ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡