የታሊባን የጸጥታ ሀይል ጺም አላሳደጉም ያላቸውን 281 አባላቱን ከስራ አገደ
“የስነምግባር ፖሊስ” የተባለው የጸጥታ አካል ከሀይማኖታዊ ስነምግባር ጥሰት ጋር በተያያዘ 13 ሺህ አፍጋናውያንን አስሯል
ታሊባን አፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ መብት ጥሰት ይወቀሳል
የአፍጋኒስታን “የስነምግባር ፖሊስ” ጺም አላሳደጉም ያላቸውን 281 የጸጥታ አባላቱን ከሰራዊቱ ማገዱን አስታወቀ፡፡
አልቃይዳን ለማጥፋት በሚል አሜሪካ ለሁለት አስርተ አመታት ጦርነት ካካሄደችባት አፍጋኒስታን በ2021 መውጣቷን ተከትሎ ስልጣን የተቆጣጠረው ታሊባን የሼሪአ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ እያስተዳደረ ይገኛል።
በዚህም “የስነምግባር ፖሊስ” በሚል ባዋቀረው የፖሊስ ሀይል ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ህጎችን የጣሱ ናቸው ባላቸው ተግባራት ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡
የምዕራባውያንን አልባሳት እና የጸጉር ፋሽን መከተልን በህግ የከለከለው ታሊባን ወንዶች “እስላማዊ ህግ” በሚያዘው መመሪያ መሰረት ጺማቸውን ማሳደግ አለባቸው ብሏል፡፡
ወንዶች ጺማቸውን ሙሉ ለሙሉ መቆረጥ ክልክል በሆነባት አፍጋኒስታን ይህን ሲያደርጉ የነበሩ 20 የወንድ ጸጉር ቤቶችን መዝጋቱና ባለሙያዎቹንም ማሰሩ ተመላክቷል።
“የስነምግባር ፖሊስ ሀይሉ” በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው መረጃ ከስነ ምግባር ጥሰት ጋር በተገናኘ ባለፈው አመት 13 ሺ ዜጎችን ማሰሩን ያስታወቀ ሲሆን “ሀይማኖታዊ ህጎችን ለማስፈጸም ያለንን ቁርጠኝነት ለማሳየት የጸጥታ አባላቶቻችንን ከስራ በማሰናበት አሳይተናል” ብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከ21 ሺህ በላይ የሙዚቃ መሳርያዎች ማውደሙን ፣ ከባህል ያፈነገጡ ፊልሞችን የሚያሰራጩ የንግድ ሱቆችን ማሸጉን እና ባለቤቶቹንም በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ አድርጓል፡፡
ታሊባን አፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሰብአዊ መብት ጥሰት ይወቀሳል፡፡
አስተዳደሩ በተለይ ሴቶች ትምህርት እንዳይማሩ ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዳይቀጠሩ እና የራሳቸው የንግድ ሱቆች እንዳይኖራቸው መከልከሉ የበርካታ አፍጋናዊያን ሴቶችን ኑሮ እንዳከበደ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም ሙዚቃ መስማት ፣ የፍቅረኞችን ቀን ማክበር ፣ የትኛውንም አይነት እንስሳት እና የሰዎችን ምስል በቤት ውስጥ መለጠፍ የተከለከለ ተግባር ነው በሚል ደንግጓል።
ተመድ ከነሀሴ 2021 እስከ መጋቢት 2024 አሰባሰብኩት ባለው መረጃ “የስነምግባር ፖሊስ” በመባል የሚታወቁት የጸጥታ አካላት ህጉን ለማስፈጸም በአንድ ሺህ 33 አጋጣሚዎች ላይ ያልተገባ የሀይል እርምጃ እና ሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን ማረጋገጡን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መጠቆሙ የሚታወስ ነው፡፡
ፖሊሶቹ ህጉን ከሚያስፈጽሙባቸው መንገዶች መካከል የአደባባይ ግርፊያ፣ ድብደባ፣ እስር እና ዛቻ እንደሚገኙበት ነው የጠቀሰው።
የሴቶች የውበት ሳሎኖችን በመላው ሀገሪቱ እንዲዘጉ ያደረገው ታሊባን ሴቶች በስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም በህዝብ መናፈሻዎች እንዳይገኙ ፣ የሚለብሷቸውን አልባሳት እና የሚንቀሳቀሱባቸውን ስፍራዎች መገደቡ ተሰምቷል።