ተመድ ታሊባን በሀይማኖታዊ ህግ ስም ተግባር ላይ ያዋላቸውን ሰብአዊ መብቶችን የሚጋፉ ህጎች እንዲያነሳ ጠየቀ
ታሊባን ሴቶች ትምህርት እንዳይማሩ ከመከልከሉ ባለፈ በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ሱቆችን እየዘጋ ነው
ከ2021 ጀምሮ በአፍጋኒስታን ስልጣን የያዘው ታሊባን የምዕራባውያን አልባሳትን እና የጸጉር ቁርጦችን በህግ ከልክሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታሊባን በሃማኖታዊ ህግ ስም የዜጎችን ሰብአዊ መብት እየጣሰ ነው ሲል አዲስ ባወጣው ሪፖርት ወቅሷል።
አፍጋኒስታን በተለይም ለሴቶች ለመኖር የማትመች ሀገር ሆናለች ያለው ተመድ ሴቶች ትምህርት እንዳይማሩ ፣ የወሊድ መከላከያ እንዳይጠቀሙ ፣ የንግድ ሱቆቻቸው እንዲዘጉ እና በመናፈሻ እና ህዝብ በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች እንዳይገኙ ክልከላ ማስቀመጡን አንስቷል።
ይህን ተላልፈው የሚገኙ ሴቶች የህጉን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ በተቋቋሙት “የሞራል ፖሊስ” በሚባሉት የጸጥታ አካላት ስድብ ፣ እንግልት ፣ ድበደባ እና እስር እንደሚፈጸምባቸው ነው የተነገረው።
በዚህ የተነሳ አፍጋናውያን ሴቶች የቻሉት ሀገራቸውን ጥለው ሲሰደዱ ቀሪዎቹ ደግሞ እራሳቸውን ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ ጨምሯል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈ አስተዳደሩ ሙዚቃ መስማት ፣ የፍቀረኞችን ቀን ማክበር ፣ የትኛውንም አይነት እንስሳት እና የሰዎችን ምስል በቤት ውስጥ መለጠፍ ፣ የምዕራባውያንን አልባሳት መጠቀም እና የጸጉር ቁርጥ ፋሽኖችን መከተል ለወንድም ለሴትም የተከለከለ ተግባር ነው በሚል ደንግጓል።
አልቃይዳን ለማጥፋት በሚል አሜሪካ ለሁለት አስርተ አመታት ጦርነት ካካሄደችባት አፍጋኒስታን በ2021 መውጣቷን ተከትሎ ስልጣን የተቆጣጠረው ታሊባን እስላማዊ የሼሪአ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ እያስተዳደረ ይገኛል።
ተመድ ከነሀሴ 2021 እስከ መጋቢት 2024 አሰባሰብኩት ባለው መረጃ “የሞራል ፖሊስ” በመባል የሚታወቁት የጸጥታ አካላት ህጉን ለማስፈጸም በአንድ ሺህ 33 አጋጣሚዎች ላይ ያልተገባ የሀይል እርምጃ እና ሰበአዊ መብቶችን መጣሳቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ፖሊሶቹ ህጉን ከሚያስፈጽሙባቸው መንገዶች መካከል የአደባባይ ግርፊያ ፣ ድብደባ ፣ እስር እና ዛቻ እንደሚገኙበት ነው የጠቀሰው።
የሴቶች የውበት ሳሎኖችን በመላው ሀገሪቱ እንዲዘጉ ያደረገው ታሊባን ሴቶች በስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም በህዝብ መናፈሻዎች እንዳይገኙ ፣ የሚለብሷቸውን አልባሳት እና የሚንቀሳቀሱባቸውን ስፍራዎች መገደቡ ተሰምቷል።
ወንዶች ጺማቸውን ሙሉ ለሙሉ መቆረጥ ክልክል በሆነባት ታሊባን ይህን ሲያደርጉ የነበሩ 20 የወንድ ጸጉር ቤቶችን መዝጋቱ እና በለሙያዎቹንም ስለማሰሩ ተመላክቷል።
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ በነጻነት የመኖር ፣ የመማር እና ሀብት የማፍራት መብትን ገድቧል ያለው ተመድ ታሊባን በሀይማኖታዊ ህጎች ቢያስተዳድርም የሰዎችን ሰበአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል ሲል መክሯል።
ታሊባን የተመድን ሪፖርት ባጣጣለበት መግለጫው ድርጅቱ አፍጋኒስታንን በምዕራባውያን ቅኝት ሊዳኝ መፈለጉ ተገቢ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።