ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ 400ሺሄክታር መሬት በሶስት አመታት ውስጥ በስንዴ አብቃይ ክልሎች በስንዴ እንደሚለማ የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል
የታንዛኒያ መንግስት ለስንዴ ልማት የሚሆን 400ሺ ሄክታር መሬት መለየቱን አስታውቋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ሁሴን ባሼ እንደተናገሩት 400ሺሄክታር መሬት ከ2022 ጀምሮ በሶስት አመታት ውስጥ በስንዴ አብቃይ ክልሎች በስንዴ እንደሚለማ ማስታወቃቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ታንዛኒያ በ2021፤ 70,000 ቶን ስንዴ ያመረተች ሲሆን ሀገሪቱ በዓመት ከ800 ሺ ቶን እስከ 1 ሚሊየን ቶን ስንዴ ከውጭ ታስገባለች።
ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሰብል ባለድርሻ አካላት በመዲናዋ ዶዶማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የግብርና ሚኒስቴር 50ሺ ቶን የስንዴ ዘር ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ላይ ነው።ከስንዴ አምራች ክልሎች የተውጣጡ የክልል ኮሚሽነሮች የጥራጥሬ ሰብል ምርትን ያለምንም ችግር እንዲቆጣጠሩ አሳስበዋል።
የሶንግዌ ክልል ኮሚሽነር ኦማርይ ምጉምባ እንዳሉት የስንዴ ዋጋ በመቀነሱ በክልሉ የሚገኙ የስንዴ አርሶ አደሮች ሰብልን ማልማት ትተው ወደ ሌሎች ሰብሎች ማምረት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የስንዴ ፍጆታዋን ከውጭ በሚገባ የስንዴ ምርት ላይ አድርጋ የነበረችው የአፍሪካ አሀጉር በስንዴ እጥረት እየተፈተነች፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ወደ ሩሲያ አቅንተው፤ ሩሲያ እህል ከዩክሬን ወደ ውጭ እንዲወጣ እንድታመቻች መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ሩሲያ ይህንኑ ለማመቻቸት ቃል መግባቷን ኮሚሽነሩ ገልጸው ነበር፡፡