የታንዛኒያ ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የታንዛኒያ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ለፍርድ እንዲቀርቡ አዘዘ
በፍሪማን ምቦዌ የሚመራው የቻዴማ ፓርቲ ክሱን ፖለቲካዊ ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል
ክሱ በቻዴማ ፓርቲ ደጋፊዎቻቸው ዘንዳ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል ተብሏል
የታንዛኒያ ፍርድ ቤት የተቃዋሚው የቻዴማ ፓርቲ መሪ ፍሪማን ምቦዌ እና ሌሎች ሶስት ተከሳሾች በሽብርተኝነት ተከሰው ለፍርድ እንዲቀርቡ አዘዘ።
የታንዛኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሙስና እና ኢኮኖሚ ሳቦቴጅ ክፍል ዳኛ ጆአኪም ቲጋንጋ የፓርቲ መሪውና ጓዶቻቸው ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ ቢያዙም ቻዴማ ፓርቲ ክሱን ከፖለቲካዊ ነው ሲል ተቃውሞታል፡፡
የቻዴማ ፓርቲ ክሱን ቢያስተባብልም ግን የመንግስት አቃቤ ህጎች የቻዴማ ፓርቲ መሪ ፍሪማን ምቦዌ እና ሶስት የቀድሞ የታንዛኒያ ወታደራዊ ወታደሮች - መሀመድ ሊንግዌንጃ፣ ኻልፋን ብዊሬ እና አደም ካሴክዋ - የሽብር ተግባራትን በማደራጀት ክስ መስርተውባቸዋል።
ምቦዌ ከስምንት ወራት በፊት በህገ መንግስት ማሻሻያዎች ላይ ለመወያየት በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ንግግር ለማድረግ በተገኙባት የምዋንዛ ከተማ ታስሯል፡፡
የምቦዌ መታሰር በደጋፊዎቻቸው ዘንዳ ከፍተኛ ቁጣ ፈጥሯልም ነው የተባለው፡፡
የቻዴማ ፓርቲ መሪ ፍሪማን ምቦዌ እና ጓዶቻቸው መታሰርን በተመለከተ የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ቲሱ ሊንዱ በግዞት በሚኖሩባት ቤልጅየም ከፕሬዝዳንት ሳሚያ ሀሰን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውም ነው የተሰማው፡፡
ሊንዱ ከፕሬዝዳንቷ ጋር በነበራቻ ቆይታ በምቦዌ ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲቋረጥ የጠየቁ ሲሆን በታንዛኒያ መንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡