“ከሁሉም ወንድ ፕሬዝዳንቶች በበለጠ የላቀ ውጤት አስመዝግቤያለሁ” - ፕሬዝዳንት ሳሚያ
ሳሚያ "የታንዛንያ ህዝብ እምነት እንዲጥልብኝ ማድረግ እጅግ ከባድ ፈተና ነበር" ብለዋል
ሳሚያ ሱሉሁ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቅ የፖለቲካ ስልጣን የጨበጡ ብቸኛ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው
የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ከሳቸው በፊት ከነበሩ ወንድ ፕሬዝዳንቶች የተሻለ አመራር መስጠታቸው ተናገሩ፡፡
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ህልፈትን ተከትሎ በወርሃ መጋቢት 2021 የሀገሪቱን በትረ ስልጣን የጨበጡት ፕሬዝዳንቷ፤ሴት በመሆናቸው ብቻ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ቀናት እምነት የሚጥልባቸው አጥተው እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
"የታንዛንያ ህዝብ እምነት እንዲጥልብኝ ማድረግና ልክ እንደ ወንድ ሀገር ምምራት እንደምችል ለማሳመን እጅግ ከባድ ፈተና ነበር" ሲሉም ተናግሯል፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለው " በመጀመርያው ዓመት ልክ ወንድ መስራት የሚችለውን በመስራት እንዲሁም ከወንድ በበለጠ በመስራት የሴትን ብቃት አሳይቻለሁ"ም ብለዋል።
ሳሚያ፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቅ የፖለቲካ ስልጣን የጨበጡ ብቸኛ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሴሬሞንያል ሚና ብቻ ያላቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳሚያ የመጡበት ወቅት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የኮቪድ ወረርሺኝን ጨምሮ በተለያዩ መሰናክሎች በተፈተነበት ወቅት ቢሆንም፤ 4 በመቶ ብቻ የነበረው የእድገት መጠን ወደ 5 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ የቻሉ እንስት መሪ ናቸው፡፡ በዚህም ሳሚያ ባለፈው ወር የ'አፍሪካ ሮድ ቢውልደርስ' ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡
በፈረንጆቹ በ2025 የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት መጠን 6 ነጥብ 7 በመቶ ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ሳሚያ ሱሉሁ፡ የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ሴት በመሆናቸው ብቻ በርካቶች ' ሀገር መምራት አይችሉም' ሲሉ እንደነበሩ በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ ነበር፡፡
ሳሚያ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አንዳንድ ሰዎች "ሴቶች የተሻሉ መሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አያውቁም ፤ ልንመራና ልናሳያቸው ግን እዚህ ተሰይመናል" ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ሳሚያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን ህልፈት ተከትሎ እ.ኤ.አ ዘመን በመጋቢት ወር 2021 በትረ ስልጣን መጨበጣቸው የሚታወስ ነው፡፡ይህም ላለፉት 7 ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩትን የ61 ዓመቷን አዛውንት ታንዛኒያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1960 በዛንዚባር ራስ ገዝ አስተዳደር የተወለዱት ሳሚያ ከ2015 ጀምሮ የማጉፉሊ ካቢኔ አባል ሆነው ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
በህዝብ አስተዳደር 2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውም ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የታንዛኒያ ፓርላማ አባልም ነበሩ፡፡ ፕሬዝዳንት ሳቢያ ባለትዳር እና የ4 ልጆች እናትም ናቸው፡፡