ንቅሳት ለካንሰር የማጋለጥ እድሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝ ጥናት አመላከተ
በ2022 አለም አቀፉ የንቅሳት ገበያ 1.89 ቢሊየን ዶላር እንደሚያንቀሳቅስ መረጃዎች ይጠቁማሉ

በንቅሳት የሚፈጠረው ካንሳር ቀለም ከሚያርፍበት ስፍራ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመስፋፋት አቅሙ ከፍተኛ ነው ተብሏል
የንቅሳት ቀለም የቆዳ ካንሰር ተጋላጭነትን እየጨመረ እንደሚገኝ የደቡብ ዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ እና የሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል።
የምርምር ቡድኑ ይህ የሚሆነው የንቅሳት ቀለም “ሊንፍ ኖድ” በተባሉ ሴሎች አማካኝነት ቀለሙ ካረፈበት ስፍራ በፍጥነት ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍል ስለሚሰራጭ ነው ብሏል፡፡
“ሊንፍ ኖድች” ሰውነትን ሊጎዱ ከሚችሉ ንጥረ ነገሮች ለመጠበቅ የሚረዱ ትናንሽ ሴሎች ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የንቅሳት ቀለም በውስጠኛው የቆዳ ክፍል ውስጥ እብጠት እንዲፈጠር እንደሚያደርግ እና ይህም ያልተለመደ የሴል እድገትን እንደሚያፋጥን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለካንሰር ሊያጋልጥ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ጥናቱ በ5900 ሰዎች ላይ የንቅሳት ንድፎችን እና የካንሰር ምርመራዎችን ካደረገ በኋላ ንቅሳት ባላቸው ሰዎች የቆዳ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የካንሰር ምልክቶች መታየታቸውን አረጋግጧል።
የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኮብ ፎን ቦርነማን ለካንሰሩ የመፈጠር እድል መጨመር የዘረመል እና የአካባቢ ሁኔታዎችን አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸው ፤ ትልቅ ወይም ብዙ ንቅሳት ያላቸው ግለሰቦች በቆዳ ካንሰር የመጠቃታቸው እድል በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ንቅሳት የተነቀሱ ሰዎች መገኛ ከሆኑ ሀገራት መካከል 48 በመቶ ዜጎቿ የተነቀሱባት ጣሊያን በቀዳሚ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
አሜሪካ በ46 በመቶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ፤ በአማካይ አንድ አሜሪካዊ 3 እና ከዛ በላይ ንቅሳቶችን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ይነቀሳል፡፡
ስፔን 42 በመቶ ፣ ዴንማርክ 41 በመቶ ፣ ብሪታንያ 40 በመቶ እና ብራዚል 37 በመቶ ዜጎቻቸው በመነቀስ በደረጃው መቀመጣቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአንጻሩ ሳኡዲ አረብያ ፣ ቱርክ ፣ ኢራን ፣ ማይናማር እና ጃፓን ንቅሳትን በሀገር ደረጃ ክልክል ያደረጉ ሀገራት ናቸው፡፡
በ2022 አመት 1.89 ቢሊየን ዶላር ገበያ ያለው አለም አቀፉ የንቅሳት ኢንዱስትሪ በ2030 የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ 3.92 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡