ቴይለር ስዊፍት የዓለማችን ቁጥር አንድ ሴት ባለጸጋ ሙዚቀኛ ደረጃን ያዘች
አሜሪካዊቷ ቴይለር ስዊፍት ሪሀናን በመብለጥ ነው አንደኛ የሆነችው
ቴይለር ስዊፍት የሀብት መጠኗ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል
ቴይለር ስዊፍት የዓለማችን ቁጥር አንድ ሴት ባለጸጋ ሙዚቀኛ ደረጃን ያዘች።
አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ቴይለር ስዊፍት የሀብት መጠኗ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ተብሏል።
ይህም ለረጅም ዓመታት የዓለማችን ቁጥር አንድ ሴት ባለጸጋ የነበረችው ሪሀና በቴይለር ስዊፍት ተበልጣለች።
ሪሀና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የነበራት ሲሆን በአንድ ወቅት የሀብት መጠኗ እስከ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር።
ስዊፍት ከ2023 ዓመት ጀምራ በተለያዩ ሀገራት በመዟዟር ያደረገቻቸው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ለገቢዋ መጨመር ዋናው ምክንያት እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
600 ሚሊዮን ዶላር ከኮንሰርቶች እንዳገኘች የተገለጸ ሲሆን ስፖቲፋይ ከተሰኘው የሙዚቃ ማሰራጫ ብቻ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ተብሏል።
ከሙዚቃንበተጨማሪም በመኖሪያ ቤት ግንባታ ኢንቨስትመንት የተሰማራችው ቴይለር ስዊፍት የ125 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከዚህ ንግድ ስራዋ እንዳገኘችም ተገልጿል።
ቴይለር ስዊፍት በ2022 "ሚድናይትስ" የተሰኘ የሙዚቃ አልበም ከለቀቀች በኋላ ያላት ተወዳጅነት ጨምሯል።
የካማላ ሀሪስ ደጋፊ እንደሆነች በይፋ ያወጀችው ቴይለር ስዊፍት በዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ዋጋ ትከፍያለሽ ተብላለች።
የ34 ዓመቷ ቴይለር ስዊፍት በመላው ዓለም ተወዳጅ ሙዚቀኛ ስትሆን ለካንሳስ ከተማ አሜሪካ እግር ኳስ ቡድን ከሚጫወተው ትራቪዝ ኬልስ ጋር የፍቅር ግንኙነት አላት።