
ሻይ ቅጠልን ለረጅም ሰዓት ማፍላት ምን ጥቅም እና ጉዳት አለው?
አዲስ የተደረሰባቸው የሻይ ጤና በረከቶች ምንምን ናቸው?
የሰው ልጅ በየዕለቱ ከሚወስዳቸው መጠጦች መካከል አንዱ የሆነው ሻይ ከውሀ ቀጥሎ በብዛት ይጠጣል።
በመላው ዓለም የሰው ልጅ በዓመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን መጠን እንደሚጠጣ ከዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
በአሜሪካው ኖርዝዌስቱርን ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት ሻይ መጠጣት ለሰው ልጆች ጤና አደገኛ የተባሉ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያስወግድ ተረጋግጧል ብሏል።
በዩንቨርሲቲው የሶስተኛ ድግሪ ተማሪ እና የጥናቱ አሳታሚ የሆኑት ቤንጃሚን ሽንዴል እንዳሉት የሻይ ቅጠሎች በተለይም በውሀ ውስጥ ያሉ እንደ ሊድ እና ብረት ማዕድናትን ከሰውነታችን በትነት መልኩ እንዲወጣ ያደርጋሉ።
በተለይም ሻይ ቅጠልን ለረጅም ሰዓት ማፍላት በውሀ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች በትነት መልኩ እንዲወገዱ ይጠቅማልም መባሉን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ጥቁር ሻይ ቅጠሎች የበለጠ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያስወግዱ የተገለጸ ሲሆን ለረጅም ሰዓት ሻይ ቅጠልን ማፍላት በተቃራኒው ጉዳት እንደሚያደርሱም ተገልጿል።
የሻይ ቅጠል መጠቅለያዎች ወይም ማሸጊያዎች ላይ የራሱ ጥንቃቄ እንዲደረግ ምክረ ሀሳቡን የሚያቀርበው ይህ ጥናት በተለይም የናይለን ወይም ከጥጥ የተሰሩ ማሸጊያዎችን ማስወገድ እንደሚገባም በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚገልጹት ሻይ መጠጣት ድብርትን ለማስወገድ፣ ሰውነታችን አካባቢውን በቶሎ እንዲላመድ፣ የምግብ ልመትን ለማፋጠን፣ የጉሮሮ እና የአፍ ውስጥ ጤናን ለመጠበቅ እና ሌሎችም ጥቅሞችን ያስገኛል።
እንዲሁም በቀን ውስጥ የተመጠነ ሻይ መጠጣት የልብ ህመምን ለመቀነስ፣ ለነርቭ እና ተያያዥ ህመሞች የመጋለጥ እድላችንንም እንደሚያስቀር ጥናቶች ይጠቁማሉ።