ቲክቶክ ላይ በምታጋራቸው ይዘቶች ያልተደሰተው ፓኪስታናዊ አባት ልጁን ተኩሶ ገደለ
አባት በልጁ የህይወት ምርጫ እና ቲክቶክ ላይ በምታጋራቸው ቪድዮዎች ደስተኛ አለመሆኑን ለፖሊስ ተናግሯል
241 ሚሊየን ህዝብ ባላት ፓኪስታን ከ54 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቲክቶክ ይጠቀማሉ
በቅርቡ ቤተሰቡን ከአሜሪካ ወደ ፓኪስታን ያዘዋወረው ግለሰብ በምታጋራቸው የቲክቶክ ቪዲዮዎች የተበሳጨባትን ታዳጊ ልጁን መግደሉን አምኗል።
የአሜሪካ ዜግነት ያለው ፓኪስታናዊ አንዋር አልሃቅ ባሳለፍነው ማክሰኞ በደቡብ ምዕራብ ኩታ ከተማ ሴት ልጁን ሂራ አንዋርን ተኩሶ መግደሉን ካመነ በኋላ በግድያ ወንጀል ተከሷል።
በ13 እና 14 አመት እድሜ መካከል የነበረችው ሂራ አንዋር ቤተሰቦቿ በአለባበሷ፣ በምትከተለው የህይወት ዘየ፣ በጓደኛ ምርጫዋ እና በቲክቶክ ቪድዮዎቿ ደስተኛ እንዳልነበሩ የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ልጁን የገደለው አባት ከቤተሰቡ ጋር በአሜሪካ ውስጥ ለ25 ዓመታት ኖሯል፤ ሟቿ ታዳጊ ከወላጆቿ ጋር ወደ ፓኪስታን ከመመለሳቸው በፊት በቲክቶክ ላይ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ስታጋራ መቆየቷ ተነግሯል፡፡
የፖሊስ መርማሪዎች የታዳጊዋን የተቆለፈ ስልክ ይዘው ለሞት ያበቃት ይዘት ምን ሊሆን እንደሚችል በማጣራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
አባት ልጁን ለመግደል ያበቃውን ምክንያት ለማወቅ ከሁሉም አቅጣጫ ምርመራ እደረገ እንደሚገኝ ያሳወቀው ፖሊስ ምናልባትም የሞቱ ምክንያት “የክብር ግድያ” ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
በፓኪስታን ውስጥ በየዓመቱ 1ሺህ የሚደርሱ ሰዎች “የክብር ግድያ” በሚባላው ምክንያት ይሞታሉ፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እነዚህ ግድያዎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት የቤተሰባቸውን ክብር ለመጠበቅ በሚሉ ዘመዶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በሴቶች ላይ እንዳነጣጠረ የተነገረለት ይህ የግድያ ምክንያት አለባባስ፣ ያላገቡ ሴቶች ከወንዶች ጋር ባላቸው ቅርበት፣ የማህበራዊ ሚድያ ይዘቶች እና ሌሎችንም ማህበረሰባዊ ህጎችን በጣሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ነው፡፡
ከዚህ ቀደም “የክብር ግድያ” የፈጽሙ ሰዎች በቤተሰቦች ይቅርታ ተደርጎላቸው በነጻ ይለቀቁ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የፓኪስታን መንግስት ከዚህ ጋር የሚያያዙ ግድያዎችን ለማስቀረት በ2016 ባሻሻለው ህግ “በክብር ግድያ” ምክንያት የሰው ነፍስ የሚያጠፉ ሰዎች በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ደንግጓል፡፡
241 ሚሊየን ህዝብ ባላት ፓኪስታን ውስጥ ከ54 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቲክቶክን ይጠቀማሉ።
በቅርብ ዓመታት ቁጥጥር ምክንያት መንግስት የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያውን በተለያዩ ጊዜያት አግዶት ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም የማህበረሰቡን እሴት እና ማህበራዊ ትውፊቶች ይቃረናሉ ያላቸውን ቪዲዮዎች ከተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እንዲወርዱ ኢስላማባድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አቀርባለች፡፡