80 ዓመታትን ያስቆጠረው፤ አንጋፋው ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
ኮሌጁ አሁን ላይ ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች መደበኛ እና አጫጭር የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል
አንጋፋውን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ “በምስራቅ አፍሪካ ተወዳደሪ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ” ለማድረግ እየተሰራ ነው ተብሏል
ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የጣልያን ጦር ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረበት ወቅት የተማሩ ሰዎች ሊያፈሩ የሚችሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች እና መሰረተ ልማቶች ማውደሙን ተከትሎ በወቅቱ የተፈጠረ ቁጭትን መነሻ በማድረግ በ1934 ዓ.ም የተመሰረተ አንጋፋ ትምህርት ቤት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
የአሁኑ የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በወቅቱ “የእጅ ብልሃት እና ኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት” የሚል ስያሜ እንደነበረውም ነው የኮሌጁ ዲን አቶ ግሩም ግርማ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡
የኮሌጁ ዲን አቶ ግሩም ቅየሳ፣ ግንባታ እና ኤሌክትሪክሲቲ ኮሌጁ ሲመሰረት የጀመራቸው የሙያ ትምህርቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ያፈራው አንጋፋው ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት
በሚሰጣቸው የትምህርትና ስልጠና ዘርፎች ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣው ኮሌጁ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሀገሪቱ የሚጫወተው ሚና እያደገ መጥቷልእንደ አቶ ግሩም ገለጻ፡፡
ተግባረ ዕድ አሁን ላይ በዘጠኝ የትምህርት ክፍሎች እና በ46 የሙያ ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ደረጃዎች እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችን የሚቀበልም ሲሆን አሁን ላይ 6 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከከተማ መስተዳደሩ ጋር በመተባበርም በየዓመቱ ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ለሚሆኑ አጫጭር ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ዲኑ ገልጸዋል፡፡
ኮሌጁ ባለፈው ዓመት ካሰልጠናቸው 1 ሺህ 64 ተማሪዎች መካከልል ለ900 (92 በመቶ) ያህሉ የስራ ዕድል ትስስር ተፈጥሯል፡፡
አቶ ግሩም በማኑፋክቸሪንግ፣ የእንጨት ስራዎች፣ ልብስ ስፌት፣ አውቶሞቲቭ፣ በንግድ መሰል ስራዎች እና ጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ለተሰማሩ ነጋዴዎች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ኮሌጁ ድጋፍ ይሰጣል ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 900 የሚሆኑ አንቀሳቃሾች ድጋፍ ማግኘታቸውንና በአሁኑ ዓመት 142 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
በተቋሙ ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች የተመረቱ ቴክኖሎጂዎችን ለኢንተርፕራይዞች ከማሸጋገር አንጻር እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኮሌጁን “በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ” ለማድረግ እየተሰራ ነው እንደ ዲኑ ገለጻ፡፡ ለዚህም ፍኖተ ብልጽግና ሰነድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ተግባረ እድ ኮሌጅ አሁን ላይ ከሚሰጠው በመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ወደ አምስት በሚደርሱ የሳተላይት መርሃ-ግብሮች እያስተማረ ይገኛል፡፡
“አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አይሲቲ፣ ጋርመንት እና ኤሌክትሪክ ሲቲ” ኮሌጂ እሰጣቸው ያሉ የሳተላይት ስልጠና መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡
ሆኖም አንጋፋው ኮሌጅ አሁን ላይ ከባድ የማሰልጠኛና ማስተማረያ ቦታ ጥበት አለበት፡፡ የተሻሉ የተግባር ስልጠናዎችን በተሻለ መንገድ ለመስጠትም ተቸግሯል፡፡ ይህ ምናልባትም ከያዘው የተወዳዳሪነት ራዕይ ጋር አብሮ ሊሄድ የማይችል ነው፡፡
ኮሌጁ ያረፈው በ22 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ነው፡፡ ይህ በቂ አይደለም፤ ቢያንስ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የቴክኒካል ስልጠና ማዕከል ያስፈልጋል እንደ አቶ ግሩም ንግግር፡፡ በመሆኑም ራዕዩን እውን ለማድረግ የሚያስችል የመሬት ይዞታ እንዲኖረው ለማድረግ ከከተማ መስተዳድሩ ጋር ለመምክር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
በርካቶችን ያፈራው አንጋፋው ተግባረ ዕድ ከተመሰረተ 80 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡