ኢራን ፣ሩሲያ እና ቻይና የ2015ቱ የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ጠየቁ
ሶስቱ ሀገራት የምዕራቡ አለም ነገሮችን ከማባበስ እንዲቆጠብ እና ወደ ስምምነት እንዲመጣ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል
ምእራባዊያን ሀገራት በቴህራን ላይ የጣሉት ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ በኢራን ኢኮኖሚ የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ጉዳት አድርሷል
በ2015 አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባቸው የኒውክሌር ስምምነት ዳግም ወደ ተግባራዊነት እንዲመለስ ቻይና፣ ኢራን እና ሩሲያ ጠይቀዋል፡፡
ቤጂንግ ሞስኮ እና ቴህራን በጋራ ባወጡት መግለጫ የምዕራቡ አለም ከመካረር ወጥቶ ለመስማማት ወደ ሚቀርቡ ሀሳቦች እንዲመጣ ስምምነቱንም ድጋሚ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ከስራ ውጭ የተደረገው የኒውክሌር ስምምነት፣ ኢራን ከሀይል አቅርቦት ባለፈ ለጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ የሚውል ምርት እንዳታመርት በምላሹ በምዕራቡ አለም እና አሜሪካ የተጣሉባትን ማዕቀቦች የሚያነሳ ነው፡፡
ቴህራን በዚህ ስምምነት የዩራኒየም ደረጃዎቿን ልትገድብ፣ አለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጄንሲም በየጊዜው በኒውክሌር ጣብያዎቿ ላይ ክትትል እንዲያደርግ ፈቃድ ለመስጠት ተስማምታለች፡፡
በወቅቱ ትራምፕ ኢራን ለጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ የሚውል ኒውክሌር እያብላላች ነው በሚል ዋሽንግተን እና ቴህራን በአዲስ ማዕቀፍ መስማማት እንዳለባቸው በመግለጽ ስምምነቱን ቀደው ጥለዋል፡፡
3ቱ ሀገራት ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ በቅርብ አመታት አለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጄንሲ ባዘጋጃቸው 9 ጉባኤዎች ላይ ተሳትፈው የስምምነቱን ተግባራዊ መደረግ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ነገር ግን ምዕራቡ አለም ለዚህ የሰጠው ምላሽ አዎንታዊ እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡
የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመቀራረብ ጊዜው አልረፈደም ያለው መግለጫ የአለም ጂኦፖለቲክስ አሁን ከሚገኝበት ውጥረት ለማርገብ ለመሰል የመቀራረብ እና የመወያየት ጥያቄዎች ምዕራቡ አለም ፈቃደኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ከኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ሙሉ ሊባል የሚችል ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ከማዕቀቦቹ መካከል የቴህራን ኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት ነው የሚባለውን የነዳጅ ሽያጭ ጨምሮ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን ለውጭ ገበያ እንዳታቀርብ ታግዳለች፤ ከሀገሪቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው ትላልቅ ኩባንያዎች ግንኙነታቸውን እንዲያቆሙ እና የኢራን የፋይናንስ ተቋማት እንቅቃሴ ላይም ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡
በዚህ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ የኢራን ኢኮኖሚ የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ጉዳት አስተናግዷል